በቤት ውስጥ እየተከበረ ያለው ፊቼ ጫምባላላ

በቤት ውስጥ እየተከበረ ያለው ፊቼ ጫምባላላ

የመንግሥታቱ ማኅበር የባህል ተቋም ዩኔስኮ በዓለም ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት የመዘገበው የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ፊቼ ጫምባላላ”  ዘንድሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ግንቦት 12 እና 13 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚከበረው በቤት ውስጥ ነው፡፡

ፊቼ ከቤተሰብና ከጎረቤት ባለፈ ሰፋ ባለ መልኩ በባህላዊ አደባባይ (ጉዱማሌ) በሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ተሰብስቦ በዋዜማና በማግሥት ብቻ ሳይወሰን በልዩ ልዩ ባህላዊ መገለጫዎች የሚከበር በዓል ነው፡፡

ይሁን እንጂ በቅርብ ወራት በዓለም የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓሉ በአደባባይ እንዳይከበር አድርጎታል፡፡ ባለፈው ሳምንት የሲዳማ የአገር ሽማግሌዎችና አያንቶዎች ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል በዓሉ በአደባባይ እንዳይከበር መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

በሲዳማ ዞን በሚገኙ ወረዳዎችም ሆነ በጉዱማሌ ምንም ዝግጅት እንደማይደረግ ቄጣላን ጨምሮ ባህላዊ ክዋኔዎች እንደማይደረጉም ተገልጿል፡፡

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ገጹ እንደገለጸው፣ በሲዳማ አስተዳደር ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የፊቼ ጫምባላላ በዓል አያንቶዎች ባስቀመጡት መሠረት በቤታቸው ለማክበር ተዘጋጅተዋል፡፡

በዓሉን አስመልክቶ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ ፊቼጫምበላላየፍቅርናየመተሳሰብተምሳሌትእንደመሆኑ፣በዚህወቅትኮቪድ-19 ባስከተለውጫናየተነሳኑሯቸውየተናጋባቸውንወገኖችበያሉበትአለሁላችሁበማለትናየሚፈልጉትንድጋፍሁሉበማድረግከጎናቸውልንቆምናልንታደጋቸውይገባል ብለዋል፡፡

ፊቼ ጫምባላላና ነባሩ አከባበር

ስለፊቼ ጫምባላላ በዓል ምንነት በዞኑ ተዘጋጅቶ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ተደራጅቶ ወደ ዩኔስኮ ከተላከው ሰነድ የተገኘው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

‹‹ፊቼ›› በሲዳማ ባህል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ከሁለት ሳምንት ላላነሰ ጊዜ በድምቀት የሚከበር ሲሆን፣ አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሒደትና በደረጃ እየሰፋ የሚሄድ የጋራ የአከባበር አንድምታ ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ፊቼ በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚያበቃ ሳይሆን፣ ከዚህም በሰፋ መልኩ በባህላዊ አደባባይ (ጉዱማሌ) በጋራ በድምቀት የማክበር ሒደትን ያካትታል፡፡ 

ለአከባበሩ እያንዳንዱ ቤተሰብ በቅድሚያ እንደ አቅሙ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ከዚሁ አንፃር የቤቱ እመቤት ለበዓሉ ቅቤ ታጠራቅማለች ወተት በታጠነ ማለፊያ ‹‹ቁሹና›› (የወተት ዕቃ) ታከማቻለች የእንሰት ውጤት የሆነውን ቆጮ ለበዓሉ በሚሆን መጠንና ጥራት ከወዲሁ ታሰናዳለች፡፡ 

አባወራው በፍቼ ማግሥት (በጫምባላላ) ዕለት ለከብቱ የሚያበላውን ቦሌ ያዘጋጃል፡፡ ልጃገረዶች ለበዓሉ መዋቢያ ለእግሮቻቸውና ለእጆቻቸው ጣቶች ቀለበት፣ ለፀጉራቸው መሥሪያ ‹‹ሄቆ›› (የተለያዩ ቀለማት ያሉት የቱባ ክር)፣ ጨሌ፣ ለአንገታቸው ቡሪቻና ዶቃ የጌጥ ዓይነት ለፀጉራቸው ማሸሚያ ግንባራቸው ላይ የሚያስሩትን በእራፊ ጨርቅ ላይ ደርድረው የሚሰፉትን ኢልካ (አዝራር) ወዘተ. የመሳሰለውን ያስገዛሉ እግራቸውና እጃቸው ላይ የሚቀቡትን እንሶስላ ያዘጋጃሉ፡፡

የፊቼ ዕለት በዕለተ ቃዋዶ በዓሉ መከበር የሚጀምረው ከአመሻሽ ጀምሮ ነው፡፡ ለዚህም በቅቤ የራሰ ‹‹ቡሪሳሜ›› ከቆጮ የተሠራ ባህላዊ ምግብ ‹‹በሻፌታ›› (ከሸክላ በተሠራ ባህላዊ ገበታ) ቀርቦ በወተት በጋራ የመመገብ ሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን፣ አመጋገቡ የሚጀምረው በአካባቢ ከሚገኝ አንጋፋ ወይም ጪሜሳ (ብቁ አረጋዊ ቤት) በመገኘት ገበታው ከቀረበ በኋላ ለቡራኬው ሁሉም እጁን በገበታው ትይዩ በመዘርጋት ‹‹ፊቼ ከዘመን ዘመን አድርሽን›› በማለት አንጋፋው የሚሰነዝረውን ቡራኬ ቃል በጋራ በማስተጋባት አመጋገቡ ይጀምራል፡፡ ለመመገቢያ በቅድሚያ ለሁሉም በእሳት ሙቀት ተለብልቦ የለሰለሰ ኮባ ስለሚታደል አንጋፋው በኮባው ከገበታው በመጨበጥ ከጀመረ በኋላ በጋራ የመመገቡ ሒደት ይጀምራል፡፡ በፊቼ ዕለት በየቤቱ የሚቀርበው ገበታ ውስጥ ሥጋ አይካተትም፡፡ የዚህ ዓይነተኛው ምክንያት ከብቱም በሰላም ከዘመን ዘመን መሸጋገር ስላለበትና ሲዳማ ለከብት ከፍተኛ ግምት ያለው በመሆኑ ነው፡፡

ቀደም ሲል ታርዶ ሲበላ የተረፈ ሥጋ እቤት ውስጥ ካለ በዕለቱ ሥጋው ከቤት ውጪ እንያዲያድር ይደረጋል፡፡ አባወራ (የቤቱ ባለቤት) በፊቼ ዕለት ከቤቱና ከቤተሰቡ ተለይቶ ሌላ ጋር አያድርም፡፡ በዚህ ዕለት በየደጁ ከእርጥብ እንጨት ‹‹ሁሉቃ›› የተሰኘ መሹለኪያ ተዘጋጅቶ አስቀድሞ አባወራው በሁሉቃው ውስጥ ከሾለከ በኋላ ቤተሰቡንና ከብቱን ያሾልካል፤ ይህም በሰላም ከዘመን ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ነው፡፡ 

የጫምባላላ አከባበር

‹‹ጫምባላላ›› በፊቼ ማግሥት በዕለተ ቃዋለንካ የሚከበር ሲሆን፣ የፊቼ ዕለት በጋራ በተበላበት ‹‹ሻፌታ›› (ባህላዊ ገበታ) ውኃ ተሞልቶ ጠዋት ላይ አባወራውና ቤተሰቡ በውኃው ፊታቸውን በማስነካትና ከዚሁ ጋር የቀረበውን ቅቤ አባወራው እየቆነጠረ የራሱንና የቤተሰቡን አናት በማስነካት ወደ አዲሱ ዘመን የመሸጋገር ተምሳሌት ይከናወናል፡፡ የ‹‹ጫንባላላ›› ዕለት መሬት የማረስ እንጨት የመስበር የመሳሰለውን ተግባር ስለማይከናወን ለማገዶም ቢሆን አስፈላጊው እንጨት አስቀድሞ ይዘጋጃል፡፡ በዕለቱ አባወራው ከብቶቹን ማለፊያ ‹‹ካሎ›› (የግጦሽ ሳር) ውስጥ አሰማርቶ ለከብቱ ቦሌ ነስንሶ እያበላ ከብቱን አጥግቦ ያውላል፡፡ በዚህ ዕለት ልጆች ተሰባስበው በየቤቱ በመሄድ “አይዴ ጫምባላላ” እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ የቤቱ ባለቤቶች ምላሹን ‹‹ኢሌ ኢሌ›› ከዘመን ዘመን ያድርሳችሁ በማለት ልጆቹን አጥግበው ያበሏቸዋል፡፡ አናታቸውን ቅቤ ይቀቧቸዋል፡፡ በዚህ ዕለት ልጆችንም ሆነ ከብትን በአርጩሜ መምታት ነውርና አይደረጌ ነው፡፡

ከጫምባላላ ቀጥሎ ያለው የአከባበር ሒደት በጥቅሉ ሻሺጋ ሲሆን፣ ሻሺጋ በዓሉን በጋራ በገበያ እንዲሁም በጉዱማሌ (ባህላዊ አደባባይ) በድምቀት የማክበር ሒደት ነው፡፡ በአከባበሩ ከታዳጊ ወጣቶች ጀምሮ እስከ አረጋውያን ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በጎሳ በጎሳ ሆኖ ቄጣላ (ባህላዊ ጭፈራ) ከጫምባላላ ማግሥት (ዴላ) ጀምር እስከ ቀዋላንካ ድረስ ማለትም ለተከታታይ አራት ቀናት በጋራ በመሆንና ጦርና ጋሻ በመያዝ ይጨፍራሉ፡፡ የቄጣላ ዘፈን የውዳሴና የተቃውሞ ስሜቶች ይንፀባቀሩበታል፡፡ መሪዎች እንደ ሥራቸው ይወደሱበታል ወይም ይወቀሱበታል፡፡ የቄጣላ ጨፋሪዎች በየተራ ወደ ጉዱማሌ ገብተው በመቀመጥ በጎሳ መሪው ምረቃት ከተካሄደ በኋላ በአሮጌው ዘመን በኅብረተሰቡ ዘንድ የታዩ በጎ ነገሮች እንዲጎለብቱ አስከፊ የሆኑት እንዳይደገሙ ምክር አዘል መልዕክት ይተላለፋል፡፡ ዘመኑ የሰላም የብልፅግና የልማት ይሆን ዘንድ ቃለ ቡራኬ ይሰጣል፡፡ ከቄጣላ ጭፈራ ጎን ለጎን ሆሬ (የልጃገረዶች ጭፈራ)፣ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ተመራርጠው በጋራ የሚጨፍሩት ባህላዊ ጭፈራ (ፋሮ) ለወራት ይቀጥላሉ፡፡ ያላገቡ ወጣቶች በተለይ በፋሮ ጭፈራ አጋጣሚ እርስ በርስ የመተዋወቂያ መድረክ ያገኛሉ፡፡ ይህ ወቅት ተሞሽረው የቆዩ ሴቶች አምረውና በአማቾቻቸውና በጎረቤቶቻቸው ታጅበው ወደ አደባባይ የሚወጡበትና ከዘመድ አዝማድ የሚገናኙበት እንዲሁም ሙሽርንታቸው የሚያበቃበት ወቅት ነው፡፡ የቄጣላ ጭፈራ የፈረስ ግልቢያ የጉግሳ ውድድር የሚታይበት ነው፡፡ በዚሁ ወቅት ያገቡ ሴቶችና ወንዶች የሚጨፍሩት ባህላዊ ጭፈራ ሐኖ የሚሰኝ ሲሆን፣ ይህም በሲዳማ ብሔር ዘንድ ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች በሚከናወኑበት ወቅት ሴቶችም እኩል ተሳታፊ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ የሻሺጋ መደምደሚያ ላይ ፊቺ ፋሎ ወይም የፊቼ መጠናቀቅ የሚያመላክት ቄጣላ የደረጋል፡፡ በዚህም ወቅት ኅብረተሰቡ በየጎሳውና በየጉዱማሌው የሚጨፍር ሲሆን፣ በጎሳው አዛውንቶች ፊቼ ጄጂ (ፊቼ ለዘለላም ትኑር) በማለት አዛውንቶች ለማሳረጊያ በሚሰጡት ቡራኬ የፍቼ በዓል ማጠቃለያ ይሆናል፡፡ 

ፊቼ ፋሎ

‹‹ፊቼ ፋሎ›› የፊቼን በዓል በጋራ በባህላዊ አደባባይ በድምቀት የማክበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ስለሆነም በአመዛኙ የፍቼ ዕለተ ቀን በተከበረ በሦስተኛው ቀን ወይም አንደ አካባቢው በተመረጡ ቀጣይ ቀናት ‹‹ፊቼ ፋሎ›› ወይም (ሻሻጋ) በባህላዊ አደባባይ በጋራ ይከበራል፡፡ አደባባዩ ‹‹ጉዱማሌ›› ይባላል፡፡ ‹‹ጉዱማሌ›› የፍቼ በዓል በጋራ የሚከበርበትና እንዲሁም በሌላ ጊዜ የጎሳ መሪዎችና ‹‹ጭሜሳዎች›› (ብቁ አረጋውያን) ልዩ ልዩ ባህላዊ ሥርዓት የሚያከናውኑበት የተከበረ ባህላዊ ሥፍራ ነው፡፡ ኅብረተሰብ በዓሉን ለማክበር በጎሳ በጎሳ በመሆን በተለያየ ባህላዊ ጭፈራና ባህላዊ አልባሳት አጊጠው ወደ ‹‹ጉዱማሌ›› ይጓዛሉ፡፡ ሁሉም በጋራ በየጎሳው ወደ ‹‹ጉዱማሌ›› ከገቡ በኋላ የባህላዊው ሃይማኖት አባቶችና የጎሳ መሪዎች እንደ ማኅበራዊ ደረጃቸው በየተራ ንግግር ያደርጋሉ፣ ይመርቃሉ፣ ባሮጌው ዘመንና በአዲሱ ዘመን ላይ ያተኮሩ መልዕክቶች ያስተላልፋሉ፡፡ በጎው እንዲጎለብት አስከፊው እንዳይደገም ምክር አዘል መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ዘመኑ የሰላም፣ የብልጽግና የልማት ይሆን ዘንድ ቃል ቡራኬ ያደርሳሉ፡፡