አበራ ለማና ልጅነት

አበራ ለማና ልጅነት

አበራ ለማና ልጅነት

በናትናኤል ወዲ…

የአዲስ አመትን መምጣት ሊያበስሩ የሰላሌ ጎረምሶች በአንዲት መንደር ተሠባስበዋል ። መንደሯ ጉዳ አሊ በመባል ትጠራለች ። ይህች መንደር የአዲስ አመት ብርሀን ዉጋገን ልትፈነጥቅ ሽር 

ብትንብላለች ፤ ሙሽሮችዋ ጎብዬዎችም ( በሰላሌ ኦሮም ባህል እንቁጣጣሽ ሲደርስ የሚጨፈር ጭፈራ ዜማና የወጣቶቹ መጠሪየ) መንደሩን በጭፈራ እያደመቁ ኦቦ ለማ ደግፌ ቤት ደርሰዋል ፤ ወጣቶቹን አቶ ለማ ባይኖሩም ወ/ሮ ማጫሽወርቅ ተቀብለዋቸዋል ። በሰላሌ ባህል መሠረት አዲስ አመት ሲጠባ ብስራቷን የሚያፈኩ ወጣቶች ጎብዮ ጎባብዮ የሚል ዜማ እያዜሙ ወደ መንደሩ አባወራ ቤት ይተማሉ ፣ እየዘፈኑና እየጨፈሩም ቤተሠቡን ያዝናናሉ ፤ ቤተሰቡ ልጅ ቢኖረዉም ባይኖረዉም የወደዱትን ስም ለቤተሠቡ ይሠጣሉ ፣ በባህሉ መሠረትም ያ ቤተሰብ ጎቢዮዎቹ የሠጡትን ስም ተቀብሎ የልጁ መጠሪያ ያደርገዋል

 ዘመኑ ጣሊያን የራስ አስራተ ካሣ ልጆች( አበራና አስፋወሠን ካሣ) በመባል የሚታወቁ አርበኞችን ሰቅሎ ከገደለበት እምብዛም ያልራቀ ነዉና አበራም ይሁን አስፋወሰን የሚል መጠሪያ ከወጣቶች አፍ አልጠፋም ነበር ፤ ያ አባ አበራ ፣ የ ሀደ አበራ ወይም የአበራ አባት ፣ የአበራ እናት ብለዉ ወ/ሮ ማጫሽወርቅን መረቋቸዉ ፤ በወቅቱየአንድ ወር ቅሪት የነበሩት ደርባባ እመቤት አሜንታቸዉን አከሉበት 

በቃ ! ግንቦት አንድ የተወለደዉን ህፃን  አበራ አሉት ፤ የዛሬዉ ዝነኛ ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ስም የተፀነሠዉ እንዲህ ... በጎቤዎች አእምሮ ውስጥ ነበር

በስልክ የቤቱን አንፃራዊ መገኛ ሲነግረኝ እንኳንስ የሚያዉቀዉ ማያዉቀዉም ስለ ደራሲነቱ ይመሰክራል ። በጠቆመኝ መሠረት ደጃፉ ላይ ተከሰትኩ፤ በማላዉቀዉ መንገድ ዝልዝሉን ስጋ እንግዳ ሸክላ ላይ እያጋደመ አወጋኝ ። ለተከበረ እንግዳዉ የፖርቹጋል አጠባበስ ዘዬ መርጦ እንደሚጋብዝ ሲነግረኝ ፈገግ እያለ ነበር ፤ ይህቺ ፈገግታ ግን ለተለየ ከሚለዉ ሠዉ ባሻገር የምትሰጥ የበጎነቱ ሽራፊ ነች፤ ማዕዳችን ላይ የፈረንሣይ ወይን ታከለበት። ዉድ አንባቢያን ለስጋዬ ወይኑን ለነፍሳችን እንደ ወይን የሚጣፍጠዉን የአበራ ለማ የልጅነት ጣፋጭ ወግ ተጋበዙልኝ

         አፍላ ልጅነት

ያኔ በአፍላነቴ ከእረኝነት ሳይንስ ዉጪ ትምህርት እንግዳ ነበረች ። ይልቁንም መዝናናትን የዕለትተለት የህይወት ክስተት አደረግነዉ ። አይ ልጅነት .... በቃ ሁሉን ማፍረስ ፣ መስራት ፣ ደግም ማበላሸት እንዲሁም መገረፍ ፤ ቁልቋል ላይ ያለዉንእሾህ አስወግደን እንቀመጥበታለን ከዚያ ሸርተቴ ፣ ሁለት በሀ ድንጋይ በስል መጥረቢያ ክብ ቅርፅ ሠርተን መሀሉን በስተን እንጨት መክተትና እርስበርስ አንዱ አንዱን እንዲሸከም የሚያደርግና የሚሽከረከር መኪና መሣይ ነገር ፈጥረን አዲስ ነገር የመምከር አቅማችንን እንፈትሽበታለን ፣ ከልም አፈር በተሰራ ብይም ዉራ እንባባል ነበር፤                                                                                                                

              አንድ ቀን ከሚያጫዉቱኝ ጓደኞቼ መካከል አዲስ ቃል ሠማሁ፤ "ትምህርት የሚባል ነገር እኮ አለ ለምን አንሄድም? አለኝ" ተከተልኩት፡፡

             ህፃናት የሚንጫጩበት ፣ ልጆች ተከፋፍለዉ ሀ ሁ የሚሉበት፣ አንዳንዶቹ መልክተ ዮሀንስ የሚደግሙበት፣ አናታቸዉ ላይ የጠመጠሙ ኮስታራ ሠዉናእንጨት ይዘዉ ፊደል የሚያስደግሙ የምሉት ክፍል ገባሁ፤ ምን ተዐምር ነዉ? አልኩኝ፤ ደነገጥኩ ። ከዚህ አስማት መሳይ ነገር ማምለጥ እንዳለብኝ ለራሴ ነገርክት ። ቀስብዬ ወደ በሩ ተጠጋሁና ተፈተለኩ።

                እቤት ስገባ እናቴን አገኘኀት ። እናቴ ማለክለኬን አይታ ምን ሆነህ ነዉ? አለችኝ ፤አስማታዊና አስደንጋጭ  ቋንቋ ሰምቼ ተረበሽኩና አመለጥኩ ብዬ ስነግራት እናቴምቀለም ያልዘለቃት ስለነበረች አበጀህ የኔ ልጅ ከሚያስደነግጥህ ነገር እንኳን አመለጥክ አለችኝ

                  ይህን የሠማዉ አባቴ በሌላ ጊዜ የኔታ ጥዑመ ልሳን የተባሉ አይነ ስዉር መምህር አስመዘገበኝ ። ሀሁን ማጥናትና መድገሙን ከእኩዮቼ ጋር ቀጠልኩ ፤ ሆኖም ቀናት ሲደጋገሙ ሠለቸኝ ፣ ለራሴም የእረፍት ጊዜ ሠጠሁ ፤ ተማሪ ቤት ፊደል መቀመሩን ትቼ በዚያን ጊዜከሲጋራ ፓኮ የምንሠራዉ ካርታ ነበርና እሱኑ ስናደራዉ ፣ ካርታዉን እየተጫወትን አባቴ መጣ፣ ምን ትሠራለህ እዚ ? ጓደኞችህ እየተማሩ አለኝ ፣ ማረፍ ፈልጌ ነዉ ዛሬ ስለዉ እጄን አንጠልጥሎ ወደ የኔታ ወሠደኝ ። በወቅቱ የአናደደኝ ከጨዋታ መናጠቤ ነበር ፣ እየጎተተ ወስዶ እየተጫወተ አገኘሁት ብሎ ለየኔታ አስረከበኝ ። የዚያኑ ቀን ተምረን ከጨረስን ቦሀላ አባታችን ሆይና እመቤታችን ሆይ የሚለዉን ፀሎት እንደሁልጊዜዉ ድምፃችንን ከፍ አድርገን አጠናቀቅን ሆኖም አንድ ነገር ይጎለን ነበር ፤ መስነጠስ ፣ የኔታ የሚያስንቀኝ አንዲት ሶረኔ መሣይ ወይም የእንጨት ፍቅፋቂ እንዲሁም እንደበርበሬ የሚያቃጥል ነገር ሳቡ ይሉናል ፤ ነገርዬዉን የምንስበዉ አእምሮ የከፍታል ብለዉ የኔታ ስለነገሩን ሲሆን እሰከ ሰርናችን ሳብ ፣ሳብ ስናደርገዉ ክፍሉ ዉስጥ የነበርን ህፃናት ግማሹ ንፍጥ በንፍጥ እኩሌታዉ ደግም ያስጥሳል ፤ ይህ የእለቱ ትምህርት ማብቂያ ሲሆን እኔን ግን የኔታ እንድቀር አደረጉኝ ።

            የኔታዉ እዛዉ ቀን ስማርበት የነበረዉ ቦታ ላይ በአንዱ በአገልጋያቸዉ በኩል እጄም እግሬም እንዲታሰር አደረጉ ። ጫፉ ላይ ብረት ባለዉ አለንጋ ሲጥ ፣ ሲጥ ሲጢጥ የሚል ደምፅ እየማሁ በለቅሶ ግርፋቴን አደመጥኩ ። ገርፈዉኝ ሲጨርሱ ፈቱኝ ። እዛዉ እንድተኛ አደረጉ ። ተኛሁ ። በተኛሁበት ቅፅበት ታዲያ የሚያምር የዶሮ ወጥ ሽታ ደረሠኝ ፤ ሽታዉ ብቻ ሳይሆን ወጡም በትኩስ እንጀራና ትልቅ ቅልጥም ተጀቡኖ ግርፋት ያመነመነዉን ከርሴን ቀሰቀሰልኝ ፣ አልማርኩትም ፤ የበደለኝ እህሉ ይመስል ተበቀልኩት ፤ በማግስቱ የሆነዉን ለወዳጆቼ ነገርኳቸዉ ፣ቀኑብኝ ፣ እንደ ዕድለኛም ተቆጠርኩ እኔ ግን ለዘላለም አለም እንደፈቀደችና ይሁን እንዳለች የምኖርባት እንጂ በፈቃዴ ያሻኝ የምከዉንባት ምህዋር እንዳልሆነች ትምህርት ወሠድኩኝ ፤ ከዚያ ጊዜ ቦሀላ ክፍል አልቀርም ስራም አላረፈድኩም

 ለማ በገበያና ትምህርት

ለማ በገበያ በኛ ዘመን ተነባቢ መፅሀፍ ነበር፤ ለኔ ደግም የመጀመሪያ መፅሀፌ ሲሆን ያየሁትም እናቴ ዘመናዊ  ትምህርት ልታስመዘግበኝ ት/ቤት ይዛኝ የሄደች ቀን ነበር ። ት/ቤት ሲገባ ፈተና አለ በተለይ ማንበብ እንደምንችል እና እንደማንችል ለማረጋገጥ መፅሀፍ ያስነብቡን ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ነበር ለማ በገበያን የተዋወኩት ፤ ይሄማ ቀላል ነዉ ፣ አባቴን በገበያ እንደማለት ነዉ ብዬ አነበብኩት ፣ ፈታኞቹ አንተማ ቦታሁ ሁለተኛ ክፍል ነዉ ተብዬ በአበራና አስፈወሰን ት/ቤት የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆንኩኝ ፤ ከሂሳብ ትምህርት ዉጪ በእዉነት አስኳላ ለኔ አዳልታልኝ እኔም አዳልቼላታለሁ

 መዘዘኛዋ ጫማ

ክረምት በመጣ ቁጥር አዲስአበባ ካለዉ አጎቴ ጋር አሣልፍ ነበር ፤ ቤቱ ፈረንሣይ ለጋስዮን አከባቢ ሲሆን መፅሀፍ እየገዛ ያስቀምጥልኛል ፣ የገዛዉን መፅሐፍ  ማንበብ እወድ ነበር ፤ ያነበብኩትን ፊቼ ስሄድ መተረክ ደግም ደስታን በዉስጤ መፍጠር ጀመረ ።

            አንድ ቀን አጎቴ ሳላስበዉ ራንግለር የተባለ ጅንስና ሸራ ጫማ ገዝቶ ምክረዉ! አለኝ፡፡ ስሞክረዉ ልክክ አለ፡፡ ገጭ አድርጌዉ ወጣሁ፡፡ የፈረንሣይ ለጋስዮን ልጆች አሳየኀቸዉ ፤ ሆኖም ከራሴ ሸራ ይልቅ የፈረንሳይ ልጆች ሸራ ወደድኩት ፣ የወደድኩት አስተሣሠራቸዉን ሲሆን ያላየሁትና ብርቅ ሆነብኝ ፤ ብርቅ የሆነብኝ አስተሳሰር የፈረንሣይ ልጆች አስተማሩኝ ፤ በዚህ መንገድ አዲስአበባ የዘመናዊነት አልፋና ኦሜጋ አስተዋወቀችኝ ፣ ወደ ፍቼ ተመለስኩ፡፡

              ትምህርት በምንጀምርበት የመጀመሪያ ቀን በራንግለሬ ሽክ ፣ በሸራ ጫማዬና በአስተሣሠሩ ፍክት ብዬ ወደ ት/ቤት ለጓደኞቼ የለበስኩትን ለማሣየት ፣ ያነበብኩትን ለመተረክና አዲስአበባ እነሡ ያላዩትን ለማሳየት ፈጠንኩ ታዲያ አንድ ወፍጮ ቤት የነበራቸዉ የሠፈሬ ጎረምሣ በጫማዬ አስተሣሠር ተደምሞ አስቆመኝ ፣ ማሠር እንደሚችልም ነገረኝ ፣ አትችለዉም አልኩት ፤ ካሠረዉ 10 ሣንቲም ልሠጠዉ ካላሠረዉ ግን ሊሠጠኝ ተስማማን ፣ ሊያስረዉ አልቻለም ፤ አልቻልክም ተበልተሀል አልኩት ። "አልሰጥህም አለኝ ፣ ቃልህን ጠበቅ  አልኩት ጭራሽ ሊመታኝ ተንደረደረ ፤ ተደባደብን ፤ ድንገት ትራሡ ዉስጥ ያለዉን ሽጉጥ አስታወስኩ ፣ እገድለዋለሁ ብዬ ዛትኩ ፣ እጄን ትራሡ ዉስጥ መሰስ አድርጌ ከቤት ወጣሁ ፣ ሽጉጤን ይዤ ወደ ልጅ ሮጥኩ ፣ ሽጉጡን ሲያይ ያ መለሎ ከመቅፅበት ወደ ወፍጮ ቤቱ ሸሸ ። እኔም ባረኩት ነገር ደስ እያለኝ ፍከርኩ ። ወደ ላይ ብተኩስ እራሱ ደስ ይለኝ ነበር

              ወደ እናቴ ተመለስኩ:: የሆነዉን ሁሉ አንድም ሳላስቀር ነገርኳት:: "ቃሉን አልጠበቀም? ጭራሽ አስፈራራህ?" አለችኝ ፣ በአዎንታ ራሴን ነቀነኩኝ ፣ "ታዲያ ምን አደረክ?" አለችኝ ፣ አልገደልኩት ግን አስፈራራሁት ስላት " ደግ አደረከዉ ልጄ ቃሉን ካልጠበቀ አበጀህ ይበለዉ" ብላ አበረታታችኝ ፤ ሆንም የ ሽጉጥ ማዉጣቴ ስለታየና ልታሠር ስለምችል ከተማ ስለመቀየር ከእናቴ ጋር ወሠንን ።

              ጫማዬ በስብሷል፤ እንዲደርቅም እንጀራ ከሚጋገርበት ምጣድ ጎን አስቀመጥኩት፤ ስለ ት/ቤት መቀየር እያወራሁ እናቴ አንድ ሀሳብ አመጣች ፤ "ጎሀ ፅዮን አክስትህ ጋር ነገ ሂድና ተማር ባሏም ይረድሀል" አለችኝ ፤ እያወጋን የጨሰ ነገረ ሸተተን ፣ ደነገጥኩ ያ መከረኛ ጫማ ነዉ ብዬ ወደምጣዱ ሮጥኩ ፣ የሸተተን የተቃጠለዉ ጫማ ጫፍ ነበር ፤ ተበሣጨሁ ፤ ሆኖም ሁለቱም እግር አንድ አይነት እንዲሆን ሁለቱንም እኩል በተቃጠለዉ ልክ ቆረጥኩት

               የተቆረጠዉን ጫማ ተጫምቼራነሸግለሩን ቂቅ ብዬ አክስቴ ካለችበት ከተማ ሄድኩ ። የአክስቴ ባልም መምህር ስለነበርወደ ከተማወ እንገባሁ ት/ቤት ተመዘገበኩ ፤ የገባሁበት ት/ቤት ተማሪዎች ፀጉረ ልዉጥ ሆኜባቸዉ ይሁን ባለባበሴ ተገርመዉ ከበባ ፈፀሙብኝ

             በማግስቱ ጠዋት ሠልፍ ስነስርዐት ላይ ስሜን ጠራ፤"አበራ ለማ የተባለ ባለጌ ተማሪ የት/ቤቱን ተማሪዎችበሙሉ ጫማቸዉን አስቆርጧል ፤ አስር ተገርፎ መባረር ይገባዋል" ብሎ ወሠነብኝ ፤ እኔም ሀቅም ስላለኝ ማባረር ትችላላችሁ መምታት ግን አትችሉም ብዬ ወደ በሩ ተምዘገዘኩ ፤ በቅፅበት አንድ ፊቱ በጢም የተወረረ ስክን እርግትያለ ወጣት ትከሻዬን ዳሠሠኝ ፤ ምን እንደሆንኩ ጠየቀኝ ፣ የሆነዉን አንድም ሳላስቀር ነገርኩት ፤ስላመነኝ ለዳይሬክተሩ አሳመነዉ ፤ እኔም  ያኔ አባብሎ ወደ ት/ቤት የመለሰኝ ወጣት ኀላ ላይየህወሀት መሪ የሆነዉ አቦይ ስበሀት ነጋ በሚል የትግል ስም የሚታወቀዉ ወልደስላሴ ነጋ ነበር ፤ መምህሩ በጭራሽ መንግስቱም ኢህአዴግ እንደሚመራና የስርዐቱ ቁንጮ እንደሚሆን አላሠበዉም ነበር ፤አበራም ታላቅ ደራሲና ጋዜጠኛ እንደሚሆን እንዲሁም የኖርዌይ የመጀመሪያዉ ጥቁር የደራሲያን ማህበር አባል እንደሚሆን አላሠበዉም  ነበር

   የሆነዉ ግን እንዲያ ነበር ........