የተስፋ አድማስ - ብቻ!

የተስፋ አድማስ  - ብቻ!

…  ሶሎን ከክ.ል.በ በ630 እስከ 560 እ.ኤ.አ የኖረ አቴናዊው የህግ ፈላስፋና ገጣሚ ነው፡፡  ዛሬም ድረስ መላው አለም የሚመፃደቅበትን የዲሞክራሲ እና ህጋዊነት መሰረት የጣለ የሰው ልጆች ሁሉ ባለውለታም ተደርጎ ይቆጠራል…

የተስፋ አድማስ  - ብቻ!

በተስፋፂዮን ጋሻነህ

ሶሎን ከክ.ል.በ በ630 እስከ 560 እ.ኤ.አ የኖረ አቴናዊው የህግ ፈላስፋና ገጣሚ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ መላው አለም የሚመፃደቅበትን የዲሞክራሲ እና ህጋዊነት መሰረት የጣለ የሰው ልጆች ሁሉ ባለውለታም ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ብርቱው የህግ ሰው የአቴኒያን ዲሞክራሲ አባት ነውም ይሉታል፡፡ በወጣትነቱ ወታደራዊ መሪና ገጣሚም ነበር፡፡ ይህ ደፋር አቴናዊ የከተማ መንግስቱ(City State) ተዘፍቆበት ከበነረው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሞራል ልሽቀት አውጥቶ ወደ አዲስ መንገድ ለማስገባት ህግን፣ ስነጽሁፍንና ፍልስፍናዊ ዲስኩርን ነበር የተጠቀመው፡፡ በዚህም በአቴናውያንን የምንጊዜም ባለውለታ ከሆኑት ሠባቱ ጠቢባን (the seven wise sages) ጉባኤ ውስጥ አንዱ ሲሆን የአርዮስፋጎስ ምክር ቤት አባልም ነበር፡፡ (ስለ አሪዮፋጎስ ወደፊት ብዙ የምላችሁ ይኖራል) ነገር ግን ዛሬ ሶሎን ከአቴንስም አልፎ በሮም፤ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በመላው አለም ምትክ እንደማይገኝለት የፖለቲካ ስርዓት የሚታየውን ዲሞክራሲን በህጋዊነት ጽኑ መሰረት ላይ ለማንበር እጅግ ደክሟል፡፡ ነገር ግን ዛሬ አለም የምታመሰግነውን ያህል የዚያንዬዎቹ አቴናውያን አላመሠገኑትም ነበር፡፡ እንዲያውም እንደጠላት ነበር ያዩት፡፡

ሶሎን የህግ አውጪ ምክር ቤቱን ከፍተኛ ይሁንታ አግኝቶ ዘርፈብዙ የህግ ማሻሻያ ስራውን ከመጀመሩ በፊት አቴንስ በአፋኙ የድራኮን ህገ-ሥርዓት እየተመራች በኢኮኖሚ ድቀት፣ የፖለቲካ ወድቀትና የሞራል ልሽቀት ማጥ ውስጥ ገብታ ትዳክር ነበር፡፡ በጊዜው ተግባር ላይ ውሎ በጽኑ ክንድ ይተገበር የነበረው የሀገሪቱ ህግም የድራኮን ህግ (the Draconian law code) የሚባለው አረመኔያዊ የህግ ስርዓት ነው፡፡ (ዛሬም ድረስ ቃሉን አፋኝ ህጎችን ለመግለፅ እንጠቀምበታለን፡፡) ነገር ግን ራሱ ሶሎን የጦር አጋፋሪና የህግ ማርቀቂያ ምክር ቤት (አርዮስፋጎስ) አባል፣ የፍርድ ቤት ዳኛና አስተዳዳሪ ሆኖ በየደረጃው ያገለገለበትን አፋኝ ስርዓት አምርሮ ይጠላው ነበር፡፡ በስርዓቱ ውስጥ አነስተኛ የዲሞክራሲ ልምምድ ቢኖርም የይስሙላና አድሏዊ በመሆኑ ሶሎን ክፉኛ ተጠየፈው፡፡ በብዕር ሳይሆን በደም የሚጻፈው ይህ የህግ ስርዓት አብዛኛውን ወንጀል በሞት የሚቀጣ አፋኝና ደም አፍሳሽ በመሆኑ አቴናውያን በፍሃት ቆፈንና በባርነት ቀንበር ውስጥ እየማቀቁ ይኖሩ ነበርና፡፡

በድራኮን ስርዓተ-ህግ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን ቦታ ማግኘት የሚቻለው በደም ትስስርና በሀብት ብቻ ነው፡፡ ጥቂት ጉልበተኞች ሀገሪቱን በጨቋኝ ህግ ሰንገው ስለያዙ አብዛኛው አቴናዊ ከሰው የማይቆጠር ባሪያና የእድሜ ልክ ባለዕዳ ሆኖ ለጥቂት ጉልበተኛችና ባለመሬቶች አኗኗሪ ሆኖ ይማቅቃል፡፡ ቀስበቀስ ግፉና ጭቆናው መቋጫ ሲያጣ ፖለቲካው የአንጃዎች የስልጣን ፉክክር ሜዳ ሆነ።  አቴናም በጎሳዎች ግጭትና በጦርነት ስጋት ውስጥ ወደቀች፡፡ ኢኮኖሚው በጥቂት ግፈኞች ቁጥጥር ስር ወድቆ ስለነበረ  ንግድና ግብርናው ተዳክሞ አብዛኛው ዜጋ የጥቂቶች ባሪያ ሆነ፡፡ ይህም ነባሩን ማህበራዊ መዋቅር በማፋለስ የሞራል ልሽቀትን አስከትሎ አቴንስን ወደባሰ አረንቋ ይዟት አካለባት፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር በአፋኙ ስርዓት ውስጥ ሆኖ የህዝቡን የመከራ ቀንበር ለመስበር ቀኑን ሲቆጥር የነበረው ሶሎን በህግ ማውጫ ምክር ቤቱ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የተቆናጠጠው፡፡ ሶሎን ለረጅም ጊዜ የአቴናውያን መከራ ያንገበግበው ኖሮ የምክር ቤቱን ይሁንታ እንዳገኘ ሳይውል ሳያድር ስር ነቀል የሚባል የህግ ስርዓት ማሻሻያ (Legal system reform) ጀመረ፡፡ ጨቋኝ ህጎችን አላላ፡፡ አዳዲስ ህጎችን ደነገገ፡፡ በቀድሞው ስርዓት ለጭቆና ይውሉ የነበሩትን ሃገሪቱ ተቋማት ላይ በእውነተኛ ህግ የተደነገገ ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያ(Institutional reform) አደረገ፡፡ በሀብት ደረጃ ላይ በተመሰረተ የተዋረድ ማዕረግ ተሸንሽኖ እንደዜጋ ሳይሆን እንደ እንስሳ ይኖር የነበረው አቴናዊ ሁሉ በቀጥተኛ ተሳትፎ (Direct democracy) መሪዎቹን እንዲመርጥ የምክር ቤቱን አባላት ማሳመን ቻለ፡፡ በዚህም የተነሳ የህዝብ ተሳትፎና የምርጫ ስርዓቱ ተሻሽሎ ሁሉም ዜጋ "ኤክሌዥያ" በሚባለው የህዝብ ጉባዔ ውስጥ እንዲሳተፍና መሪዎቹን በፈቃዱ እንዲመርጥ አስቻለው፡፡ (የእውነተኛ ዲሞክራሲ ሀሁ እዚህ ጋር እንደተጀመረ ልብ ይሏል።) የእዳና የግብር ስርዓቶችንም አሻሻለ፡፡ በባርነት ደረጃ የመሬት ከበርቴዎችን ከርስ ይሞሉ የነበሩ ገበሬዎች ከጨካኝ አስዳዳሪዎቻቸው ነፃ እንዲወጡና በብድር ተዘፍቀው ጉልበታቸውን እየተበዘበዙ የሚኖሩ ዜጎች እዳቸው እንዲሰረዝላቸው የሚያስችል ህግ አወጣ፡፡ ራሱም አርዓያ በመሆን የእሱ ብድር ያለባቸውን ባለዕዳዎች ምህረት አደረገላቸው፡፡

በዚህ ሁኔታ ሶሎን የአቴንስን የህግ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በማሻሻል መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ቻለ፡፡ ብዙዎች አዳዲስ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና ነፃነቶችን ማጣጣም ቻሉ፡፡ ኢኮኖሚውም እንደገና አንሰራራ። ስልጣን ሀብት ማጋበሻ መሆኑ ቀርቶ ማገልገያ ሆነ፡፡ ነገር ግን ቀስበቀስ ተቋማት በዲሞክራሲያዊ ህግ መሰረት መመራት ሲጀምሩና አፈና ሲቀር ከዚህ በፊት ታይተው የማይታወቁ አዳዲስ ችግሮች ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ስልጣን ሀብት ማስገኘቱ እንዲቀር በመደረጉ አንዳንድ ሃላፊነቶችን ለመቀበል ብዙዎች ባለመፈለጋቸው የህዝብ ቢሮዎች ክፍት ሆነው ይቀመጡ ጀመር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ቀስበቀስ በማናለብኝነት ስሜት የስልጣን ተዋረድን አለመቀበልንና የቃላት ጦርነትን ጀመሩ፡፡ በቀድሞው የድራኮን ህግ ጊዜ ሰጥ ለጥ ብለው ይገዙ የነበሩ የበታች ሹመኞችና ዜጎች እንኳን እንዳሻቸው ለመሆን ፈለጉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጉልበት ባርነትና  የእድሜ ልክ እዳ ነጻ ያወጣቸውና ለአንድ ሰሞን “ቀንበር ሰባሪው(breaker of burdens)" የሚል የማሞካሻ ስም ይጠሩት የነበሩት ዜጎች እንኳ በለሙጡ ላይ ዞረው ማጉምረም ጀመሩ፡፡ “ህጋዊነትን” በእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መሰረት ላይ ባነበረው ስርዓት ውስጥ ህገወጥነትና ስርዓት አልበኝነት እየገነገነ መጣ፡፡

አቴናዊያን ሶሎን ደርሶበት የነበረው የሃሳብና የስልጣኔ ከፍታ ላይ አልደረሱ ኖሮ ትላንት ለምነው ያገኙት የዲሞክራሲ ፍሬ መራር ሆነባቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አቴንስን አስፈንድቆ የነበረው ለውጥ የስልጣን ጥመኞችና የመንጋ መሪዎች ወደሚዘውሩት ሌላ ዙር መከራ ውስጥ ሊገባ ሆነ፡፡ ዛሬም ድረስ አለም የሚጠቀምበትንና የተሻለ ምትክ ያላገኘለትን የፖለቲካ ስርዓት ለዜጎቹ አምጦ የወለደው አመድ አፋሹ ሶሎን ታዲያ የሚሆነውን ሁሉ እያየ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ይባስ ብሎም አዲሶቹ ዲሞክራሲያዊ ህጎችና ተቋማት እንደገና እንዲሻሻሉና በጨቋኝ ህጎች እንዲተኩ አቤቱታ ሲበዛበት አገሩን ጥሎ ጠፋ፡፡

 ሶሎን የሀገሩን ሰዎች እብደት ላለማየት ወስኖ ለአስር አመታት ያህል በግብፅና ቆጵሮስ ቆይቶ ሲመለስ አቴና ይባሰኑ ሰከራ አገኛት፡፡ ህገወጦችና የስልጣን ጥመኞች ወርቃማዎቹን ህጎች ከአፈር ሊቀላቅሏቸው እያደቡ እንደሆነ ሲያይ በየአደባባዩ እየዞረ ህዝቡን መማፀን ጀመር፡፡ ተማጽኖውን የሚሰማው ሲያጣ የቀድሞ ጦር መሪነቱ ወኔ ተቀስቅስበትና የወታደር ልብስ ለብሶ ‹ወርቃማዎቹን ህጎቼን የሚነካ ማንኛውንም ሰው በዚህ በዛገ ሳይፍ እቀነጥሰዋለሁ” ይል ጀመር፡፡ ነገር ግን መሳቂያ ከመሆን ሌላ ያመጣው ለውጥ አልነበረም፡፡ ይባስ ብሎም የራሱ ዘመዶች የሆኑት ፔሲስተራቶስ የተሠኙት እልኸኛ የስልጣን ፈላጊዎች ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ በጉልበት ስልጣን ለመቆጣጠር እየተዘጋጁ እንደሆነ ደረሰበት፡፡ የሶሎንን ታሪክ በብዛት የፃፈው አሪስቶትል በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ባይኖርም ሌላኛው ዝነኛ ፀሃፊ ፑልትራስ ግን ሶሎን ስልጣን ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ ሁኔታ እንዳይያዝ በማሰብ አንዳንድ ህጎችን ለማላላት ቢፈልግም እንዳልተሳካለት ጽፏል፡፡

በዚህም የተነሳ ሞገደኞቹ የገዛ ወገኖቹ የሶሎንን የህጋዊነት ተማፅኖ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ስልጣኑን በጉልበት (Tyranny) ተቆጣጠሩት፡፡

‹ስልጣን በህግ ብቻ!› እያለ ሲጮህ የነበረው ሶሎን ህዝቡም ሆነ ልሂቁ ሊሠሙት ባለመፈለጋቸው ሊመጣባቸው ያለው አስፈሪ ጊዜ ከሩቁ ታይቶት አቴናዊያንን ሁለት ተገቢ ስድቦችን ሰድቧቸው ሞተ. . . “ፈሪዎችና ደደቦች!”

ህግ የሰውን ልጆችን ደመነፍሳዊ ራስወዳድነትና አመጸኝነት በመግራት ወደ ፍትሃዊና (fair) የበለጸገ (prosperous) ህይወት እንዲያመሩ(Strive እንዲያደርጉ) በሰው ልጆች አዕምሮ ምናብ ውስጥ የሚጸና ስምምነት ነው፡፡ ዩቫል ኖህ ሃራሪ የተሰኘው እስራኤላዊ የታሪክ ሊቅ ሳፒየንስ በተሰኘው መጽሃፉ የመጀመርያው የተጻፈ ህግ ባለቤት የነበሩትን የባቢሎናዊያንን ህግ (የሃሙራቢ ኮድ) እና የመጨረሻውን ልዕለ ሃያል ሀገር አሜሪካን የነፃነት ድንጋጌ (declaration of independence) በጥልቀት ካነፃፀረ በኋላ ህግ ብልሁን ሰው (homo sapience) በምናባዊ የስርዓት አለም ውስጥ አስገብቶ አሁን ለደረሰበት የስልጣኔ ደረጃ ቢያደርሰውም ሣይንሳዊም ሆነ አመክኖአዊ መሰረት የለውም ብሎ ይደመድማል፡፡ ነገር ግን ዜጎቹን በማዕረግ ተዋረድ ላይ የጸና ነባራዊ ሁኔታን(factual basis) በህጋዊ መንገድ ለመምራት የተበየነውን የባቢሎን ህግም ሆነ “ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው” በሚል ፍልስፍናዊ መሰረት ላይ የጸናው እንደአሜሪካ ህገ መንግስት የሚለያዩትን ያህል ከሳይንሳዊና አመክኗዊ ብያኔ አንጻር  ሁለቱም አንድ ናቸው (በዚህ ርዕስ ላይ በሌላ ጊዜ በዚሁ አምድ የምንካፈለው ይኖራል)፡፡ የሆነው ሆኖ ሃራሪ ሰዎችን እኩል እንዲሆኑ ወይም እንዳይሆኑ የሚያደርጋቸው ‹ህግ› ነው ባይ ነው፡፡  እኩል መሆናቸው ወይም አለመሆናቸው ጊዜያቸው ለሚፈቅደው አስተዳደራዊ ስርዓተ-ማህበራቸውና የኑሮ ማሻሻል ጥረታቸው እስከጠቀማቸው ድረስ ‹ህግ› የብልሁ ሰው “homo sapience” ታላቅ ባለውለታ ነው ይላል ሃራሪ፡፡

በሀገራችንም ታሪክ ረዥም የሆነ የህግ ልምምድ አለ፡፡ ሌላውን እንተወውና ከሁለት ሺህ አመታት በላይ ሀገራችንን የመራው ሰለሞናዊው ስርወ-መንግስት በገዢ ህግነት ይጠቀምበት የነበረው ክብረ ነገስት(Glory of Kings) እና ፍትሃ ነገስት (Justice of Kings) የጊዜውን ማህበራዊ ፍልስፍና የሚመጥንና በአንፃራዊነት ከሌሎች ስረወ-መንግስታት ህጎች ጋር ሲነፃፀር የጊዜውን ነባራዊ ማህበራዊ ፍልስፍናና ስሪት (በሃራሪ ብያኔ ስሪቱም ሆነ ፍልስፍናው ትክክልም ይሁን አይሁን ህግ አይመለከተውም፣ ይህ የዝግመተ-ለውጥ(evolution) እና የሰው ልጅ ተለዋዋጭ አዕምሯዊ እድገት ውጤት ነው) የሚመጥን ነበር፡፡ ይህ ህግ ኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ አመታት ከአክሱም እስከሸዋ ድረስ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ እተፈተነች ባረገችው ጉዞ ውስጥ ተከታታይ የሆነ ወጥ ሀገረ መንግስትና የአገዛዝ ሥርዓት ባህል እንዲኖር በማድረግ ዛሬ “ኢትዮጵያ” የተባለች ነጻ፣ ባለስልጣኔና ባህል እንዲሁም ሉአላዊ ሃገር እንድትኖር (ከሌሎች እውነታዎች ጋር) የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡ የየዘመኑ ነዋሪዎች (እንደ መላው የአለም ብልህ ሰዎች (Homo Sapiens) ሁሉ) ተፈጥሯዊውና አዝጋሚው የሰውልጆች መሻሻል ጉዞ በፈቀደላቸው እውነታ ልክ በስርዓትና በተዋረድ እንዲተዳደሩና ህይወታቸውን የሚያሻሽሉበት የስልጣኔ ሙከራን እንዲያደርጉም ዕድል ሠጥቷቸዋል፡፡

በዘመናዊቷ ኢትዮጲያ ታሪክም ለይስሙላም ቢሆን የህዝባዊ ሀገረመንግስት (The essence of Republic) ሰበዞች ካሉት (ለምሳሌ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትን ማቋቋሙ) የ1923ቱ ህገ መንግስት  (በዋነኝነት ንጉሳዊውን ስርዓት የሚያነብር ቢሆንም) ጀምሮ አራት ህገመንግስቶች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ህገመንግስቶቹ የየራሳቸው የሆነ የተራራቀ ፖለቲካዊ ፍልስፍናን ስለያዙ በማሻሻል ብቻ ከየጊዜው ሁኔታ ጋር እያስታረቁ መቀጠል ባለመቻሉ የሃገራችን ህገመንግስታዊ ልምምድ ቀጣይነት ያለው እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የህገመንግስት ለውጦቹ በአንድ መሰረት ላይ የቆሙ አለመሆናቸው እስካሁን ከዘለቀው የሀገረመንግስት ግንባታ ንትርክ እንኳን አላዳኑንም፡፡

 በሂደትም ከነብዙ እንከኖቹና ጥያቄዎቹ በአንፃራዊነት በሀሳብ ደረጃም ቢሆን ዲሞክራሲያዊ መርሆችንና ድንጋጌዎችን ያካተተው የአሁኑ የኢፌድሪ ህገ መንግስት ላይ ደርሠናል፡፡

የሶሎን የህግ መርሆች ዛሬም በመላው አለም ባሉ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንከተላለን በሚሉ ሀገሮች ዘንድ ይሠራሉ፡፡ የባቢሎኑ የሀሙራቢ ህግም ሆነ የአሜሪካ ህገ-መንግስት በይዘት ደረጃ ቢለያዩም በመርህ ደረጃ አላማቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ የአሜሪካን ህገ መንግስት ብንወስድ ከመሰረታዊ መርሆቹና ድንጋጌዎቹ ማዕቀፍ ስር ህግጋቱንና ትርጉማቸውን እያሻሻለና ራሱን እየቀየረ የመጣ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ “እኩልነት”ና “ነፃነትን” እንደ ሁለት እግሮች ተጠቅሞ የቆመ ቢመስልም ህገ መንግስቱ በረቀቀበት ዘመን የባሪያ አሣዳሪ ስርዓት ነበር፡፡ ነገር ግን መሰረታዊ መርሆቹ ሳይነኩ እየተሻሻሉና እየተስተካከሉ ጊዜው በሚጠይቀው ደረጃ ትርጉም ሊሰጡ በሚችሉበት ሁኔታ ራሳቸውን እየሞረዱ በመምጣታቸው ያልተቆራረጠ የህገ ምንግስታዊነት ልምምድንና የደረጀ የዲሞክራሲ ባህልን ለአሜሪካዊያን አጎናፅፏቸዋል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ በህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች መሰረት ላይ የታነፁ ተቋማት ዘላቂነትና ተዓማኒነት እንዲኖራቸውና እየጠነከሩ እንዲሄዱ ረድቷል፡፡ አብዛኞቹ የህገ መንግስቱ አንቀፆች ጊዜው በሚጠይቀው ልክ እየተስተካከሉ እና እየተሻሻሉ ቢሄዱም የተሻሻሉበት ሥርዓት ራሱ ህገ መንግስታዊ በመሆኑ አዲስ ህገ መንግስት ማርቀቅ ሳያስፈልግ፣ ተቋማት መሰረታቸው ሳይናጋ፣ የህጋዊነት ልምምድ ጉዞው ሳይደናቀፍ  እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል፡፡ በጊዜ ሂደት ትርጉሙን የሚያጣ ህግ ለህግ ስርዓቱ አዲስ የሆኑ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ጥያቄዎችን መመለስ እንዲችሉ ተደርጎ ይሻሻላል፡፡ ነገር ግን ህግ የሚሻሻለውም ሆነ ጊዜወለድ ጥያቄን እንዲመልስ የሚደረገው በራሱ በህግ እንጂ በኢ-ህገመንግስታዊ መንገድ አይደለም፡፡ አንድን አዋጅ ለመሻር እንኳ ሌላ አዋጅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ለህገ -መንግስቶች ራሳቸው ምሉዕ እንዳልሆኑ ስለሚያውቁ የማሻሻያና የመተርጎሚያ ስርዓቶችን በውስጣቸው የሚያካትቱት፡፡ አንድን ህገ መንግስታዊ ቀውስ ለመፍታት ህገ መንግስታዊ የሆነ መፍትሄ ከመፈለግ ሰንፈን ሌላ አማራጭ ከተጠቀምን እንደገና ከዜሮ ለሚጀምር የህገመንግስትና ተቋማዊ ስርዓት ልምምድ እንዳረጋለን፡፡

አሁን ስራ ላይ ያለው የኢፌድሪ ህገ ምንግስት አርቃቂዎችም ነባርና ጊዜ የሚወልዳቸው ክፍተቶች ሊኖሩበት እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ እነዚህ ጥያቄዎች በራሱ በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲፈቱ አማራጮችን አስቀምጠዋል (የሥነጽሑፍ ሰዎች 'የማሪያም መንገድ' ይሉታል)፡፡ በህገመንግስቱ ውስጥ የማሻሻያ (Amendment) እና የመተርጎሚያ (Interpretation) አንቀጾች መካተታቸው ማናቸውንም ሥነመንግስታዊ ችግሮች ሁሉ በህግ 'ብቻ!' ለመፍታት ፍላጎት ('The Solon Syndrome' እለዋለሁ እኔ) እንደነበራቸው ማስረጃ ነው፡፡ አሁን ሀገራችን ከገባችበት የህገ መንግስት አጣብቂኝ አንፃር የቱ የህግ አማራጭ የተሻለ እንደሆነ መበየኑን ለህግ ባለሞያች ልተውና ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተነሱ ያሉ እንደ ሽግግር መንግስት ያሉ የመፍትሄ ሃሳቦች ምን ያህል ኢ-አመክኖአዊና ኢ-ህገመንግስታዊ እንደሆኑና ሀገራችንን እንደገና ወደ አረንቋ ሊከቷት እንደሚችሉ በዚሁ አምድ ስር በተከታታይ እናያለን፡፡ በተለይ ለወትሮው የህገመንግስቱ ወዶገብ ጠበቃ ነን ሲሉ የነበሩት “የመፍትሄ” አመንጪዎቹና የሃሳብ ተጋሪዎቻቸው ይዘውት የመጡት ሃሳብ እነሱ ሰክረንበታል የሚሉትን የዲሞክራሲ ወይን ጠንስሶ በጠመቀው በሶሎን አንደበት “ፈሪና ደደብ” ሊያስብላቸው የሚችል ስህተት መሆኑን በሚቀጥለው ዕትም እናየዋለን፡፡

* ብቻ ወይም ብቸኛ የሚለው ቃል “ሶለም” ወይም “ሶሎ” የሚል የላቲንና “ሞኖስ” የሚል የግሪክ አቻ ቃል አለው፡፡ ነገር ግን “ሶሎን” ከሚለው ስም ጋር የስርወቃል ግንኙነት ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ አደለሁም፡፡

 *ሶሎን በዋሽንግተን ዳሲ ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ በሚገኘው ሀውልቱ ላይ በአንድ እጁ ስለት የሌለው ሰይፉን ዘቅዝቆና ዝቅ አድርጎ የያዘ ሲሆን በሌላኛው እጁ 01-NOMO የሚል ጽሁፍ ያለበት ጥቅል ብራና ከፍ አድርጎ ይዟል። 'NOMO' የሚለው ቃል "NO MORE" ከሚለው የእንግሊዝኛ ሃረግ ጋር መቀራረቡም አጋጣሚ ይመስለኛል።