ብሩንዲ ምርጫውን ተከትሎ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ዘጋች

ብሩንዲ ምርጫውን ተከትሎ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ዘጋች

ብሩንዲያዊያን ረዥም ጊዜ አገሪቷን ያስተዳደሯትን ፕሬዚደንት ንክሩንዚዛን ለመተካት ዛሬ ምርጫ እያካሄዱ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎም የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ የሆኑትን ዋትስአፕ፣ ፌስቡክ እና ትዊተርን ዘግታለች፡፡

ማህበራዊ ሚዲያዎቹ መዘጋታቸውን ቢቢሲም ሊያረጋግጥ ችሏል፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች ማግኘት የሚችሉትም የግለሰቦችን ማንነት የማያሳየውን ቪፒኤን የተሰኘ ኔትወርክ የሚጠቀሙ ብቻ ናቸው፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁ ባለሥልጣናት ምላሻቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። በአገሪቷ የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱት ዛሬ ማለዳ ጀምሮ ሲሆን አንድ የአገሪቷ ጋዜጠኛ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ለመምርጥ የተሰባሰቡ ሰዎችን ፎቶ አጋርቷል፡፡

ፕሬዚደንቱን ለመተካት 7 እጩዎች የቀረቡ ሲሆን ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡ የምርጫ ቦርድ ኮሚሽን አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ከ53 የውጭ ኤምባሲዎች የተመረጡ ተወካዮች ምርጫውን እንዲታዘቡ ፈቅዷል፡፡ ፕሬዚደንት ንክሩንዚዛ ከሥልጣን የሚወርዱት ከ15 ዓመታት በኋላ ሲሆን፤ አዲስ ወደ ተመቻቸላቸው ኃላፊነት ይሸጋገራሉ ተብሏል፡፡

ይሁን አንጅ ምርጫው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት መካሄዱ እየተተቸ ነው፡፡ ብሩንዲ እስካሁን ከ40 በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን በቫይረሱ የአንድ ሰው ሕይወትም አልፏል፡፡ ምርጫውን ተከትሎ ሕዝባዊ ሰልፎች መካሄዳቸውም ወቀሳን አስከትሏል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት የመንግሥት ቃል አቀባዩ በቫይረሱ ሰው ባልተመዘገበበት ወቅት አገሪቷን ፈጣሪ እንደጠበቃት ተናግረው ነበር፡፡

ባለሥልጣናትም ዜጎች ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም በሚችሉት መጠን ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች እንዲታቀቡ ከመምከር ውጭ ጥብቅ የሆኑ ገደቦችን ለመጣል አልፈለጉም፡፡ በእርግጥ በምርጫው ዘመቻ ወቅት ይህም ሲተገበር አልታየም፡፡