ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ-አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር ከኮሮናቫይረስ እንዲጠነቀቅ የጤና ሚኒስትሯ አሳሰቡ

ህዝበ ሙስሊሙ የዒድ-አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር ከኮሮናቫይረስ እንዲጠነቀቅ የጤና ሚኒስትሯ አሳሰቡ

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል-ፈጥር በዓል ሲያከብር ለኮሮና ቫይረሰ ተጋላጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንዳለበት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

የጤና ሚኒስትሯ 1441ኛውን የዒድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ትናንት ባስተላለፉበት ወቅት፣ ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የረመዳን ጾም ወቅት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚያግዝ መልኩ በከፍተኛ ጥንቃቄ ማሳለፉን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በመቀበል የጁማአ ጀመአ ስግደትን በመተው በተጠናጠልና በቤት ውስጥ ሲሰግዱ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጸው፣ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች ምስጋና አቅርበዋል። ጥንቅቄው በዒድ በዓል አከባበር ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም በበዓል ወቅት እንቅስቃሴዎች ስለሚበዙ በማንኛውም ጊዜ የፊት ጭንብሎችን በማድረግና የእጅ ንጽሕናን መጠበቅ እንደሚገባም መክረዋል።

በበዓሉ ወቅት የሚበሉ ምግቦችን አብስሎ መመገብ እንደሚገባና እርድም በከፍተኛ ጥንቃቄ መከወን እንዳለበት አሳስበዋል።

 በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2012 ዓ.ም

ተጨማሪ 30 ሰዎች በኮረና ቫይረስ ተያዙ

አዲስ አበባ፦ ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 30 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገለጸ። ከኮረና ቫይረስ ያገገሙ ሰዎች 128 መድረሳቸውንም የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

 የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ባለፉት 24 ሰዓታት የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 3 ሺ 645 ሰዎች መካከል30 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸውል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው 26 ወንድ እና 4 ሴት ኢትዮጵያን ናቸው። ከ15 – 60 የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። 9 የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 17 በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲሆኑ፣ 4 የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው፣ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያልነበራቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው 18 ከአዲስ አበባ፣ 3 ከትግራይ ፣ 3 ከአፋር ፣ 4 ከኦሮሚያ ክልል ለይቶ ማቆያ የነበሩ ሲሆኑ፤ 2 የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

ባለፊት 24 ሰዓት ውስጥ 5 ሰው ከበሽታው ማገገሙን አስታውቀው፤ በአጠቃላይ በኢትዮ ጵያ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 128 መድረሱንም አመልክተዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 429 መሆኑን ጠቁመው፥ ከእነዚህም ውስጥ 294 ሰዎች በለይቶ ህክምና ላይ መሆናቸውን አስታው ቀዋል። አስከአሁን ለ73 ሺ164 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ መሠራቱንም ገልጸዋል።

በቫይረሱ የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፥ ሁለት የውጭ አገር ሰዎች ደግሞ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ አይዘነጋም።