የትምህርት ቤት ምገባና ቁሳቁስ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

የትምህርት ቤት ምገባና ቁሳቁስ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

ለ2013 የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን በመንግሽት ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች ምገባና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአፍሮ ሄልዝ ቴሌቪዥን የትምህርት በቤቴ ፕሮግራም ተሳትፈው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ወላጆች እውቅና በተሰጠበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በ2012 የነበረውን 380 ሺ ተጠቃሚ በቀጣዩ ዓመት ስደስት መቶ ሺ ለማድረስ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል። በዘንድሮ ዓመት ሲሠሩ የነበሩት የትምህርት ቤት አድሳት፤ የደንብ ልብስና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች አቅርቦት እንዲሁም የምገባ ፕሮግራም በቀጣዩ ዓመትም በተሻለ ሁኔታ የሚቀጥሉ ይሆናል። በደንብ ልብስ አቅርቦት ረገድ ለሁሉም ተማሪዎች አዲስ የደንብ ልብስ የሚቀርብ ሲሆን፤ የቀለምና የዲዛይን ምርጫም በተማሪዎች የሚወሰን ይሆናል። በተጨማሪ ተማሪዎች በመረጡት ቀለምና ዲዛይን መሰረት በባለሀብቶች ድጋፍ ከዱባይ ቦርሳ ተገዝቷል። ከስምንተኛ ክፍል በላይ ላሉ ተማሪዎችም ታብሌት የሚቀርብ ይሆናል።

ፕሮግራሙም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በዙሪያዋ ካሉ ከተሞችና ወረዳዎችም የሚጨምራቸው ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ አጠቃለይ ፕሮግራሙም ቀጣይነት እንዲኖረው ይህንን የሚቆጣጠር በከተማ መስተዳድሩ ስር መስሪያ ቤትና ቦርድ ተቋቁሟል። ከተማ አስተዳደሩ የሚያደርገው ድጋፍ ተማሪዎችን ከማብቃት ባለፈ በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጠበብ እንደሆነ የተናገሩት ኢንጂነር ታከለ መምህራንን ማብቃት የትምህርት ጥራትና ስፋት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ከንክኪ ነፃ የሆነ ትምህርት ለማዳረስ በቴሌግራም፤ በዩቲዩብ፤ በቴሌቪዥንና በድረገጾች ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። ይህም ለከተማው ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ እድሉ ላላቸው የቀውስ ጊዜ አማራጭ የትምህርት መርሐ ግብር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በርካታ ተማሪዎችም ፕሮግራሞቹን በመከታተል ውጤታማ እየ ሆኑ ይገኛሉ። በመሆኑም ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች ይህንን ዕድል በመጠቀም ልጆቻቸውን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በዕለቱ 41 የላፕቶፕና የቴሌቪዥን ሽልማቶች የተበረከቱ ሲሆን፤ በአጭረ የጽሑፍ መልዕክት የተወዳደሩ 30 ተማሪዎችና አስራ አንዱ ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ይከታተሉ የነበሩ ወላጆችና ልዩ ተሸላሚዎች መሆናቸው ተገልጿል።