ትዊተር የዶናልድ ትራምፕን ጽሑፍ ግጭት ያበረታታል በሚል እንዳይታይ አገደው

ትዊተር የዶናልድ ትራምፕን ጽሑፍ ግጭት ያበረታታል በሚል እንዳይታይ አገደው

ትዊተር ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጽሑፎች አንዱን ግጭት ያበረታታል በሚል መልዕክታቸው በገጻቸው ላይ እንዳይታይ አድርጓል።

ጽሑፉ ከገጻቸው ላይ እንዲጠፋ ባይደረግም፤ አንባቢዎች እውነተኛነቱን እንዲያጣሩ የሚጠቁም መልዕክት ተያይዞ ተለጥፏል። ትዊተር ጽሑፉን ሰዎች ለማንበብ ይፈልጋሉ በሚል ሳያጠፋው እንደቀረ አስታውቋል።

ትዊተርና የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አንድ ሁለት መባባል ጀምረዋል። በሚኒያፖሊስ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ አፍሪካ አሜሪካዊ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ ሕዝብ ተቃውሞውን እያሰማ ነው። ፕሬዘዳንቱ “የአገር መከላከያ ይላካል። ማውደም ከተጀመረ መተኮስ ይጀመራል” ሲሉ ትዊት አድርገዋል። ትዊተር “ማውደም ከተጀመረ መተኮስ ይጀመራል” የሚለውን ትዊት ነው በትራምፕ ገጽ እንዳይታይ ያደረገው።

ትዊተር ታዋቂ ሰዎች የሚጽፉትን ከማጥፋት ይልቅ ከማስጠንቀቂያ ጋር ለማውጣት ውሳኔ ያስተላለፈው ባለፈው ዓመት ነበር። ሆኖም ግን የትራምፕ ትዊቶች ላይ ሕጉ እስካሁን አልተተገበረም ነበር።

በዩናይትድ ኪንግደም የማኅበራዊ ሚዲያ ተንታኝ ካርል ሚለር “ትዊተርም ይሁን ሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲህ ድፍረት የተሞላው ተግባር ሲፈጽሙ አላየሁም” ብለዋል።

የትዊተር እርምጃ በድረ ገጽ ስለሚደርስ ጥቃት እንዲሁም ስለ ንግግር ነፃነት ያለውን ክርክር ያጦዘዋል ሲሉም ተንታኙ ተናግረዋል።

ትራምፕ በፌስቡክ ላይ ያሰፈሩት ተመሳሳይ ጽሑፍ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ተለጥፏል።

ባለፉት ዓመታት፤ ትዊተር ዶናልድ ትራምፕን እንደ ሌሎች የትዊተር ተጠቃሚዎች እንዲመለከታቸውና የተቋሙ ሕጎች ተፈጻሚ እንዲሆኑባቸው ቢጠየቅም፤ ትዊተር አንዳችም እርምጃ አልወሰደም ነበር።

ያሳለፍነው እሮብ ግን የትራምፕን ጽሑፍ “እውነታውን ያጣሩ” ከሚል መልዕክት ጋር አወጣ።

ተቋሙ የትራምፕን ትዊቶች ባወጣቸው ሕጎች መሠረት መቃኘት ወይም ካለፈው እሮብ በኋላ የተከተለውን ውዝግብ የማሳለፍ አማራጮች ነበሩት። እናም ትዊተር ሕጎቹን መከተል የመረጠ ይመስላል። የፕሬዘዳንቱ ጽሑፍ ግጭትን የሚያበረታታ ማለቱም ውሳኔውን በግልጽ ያሳያል።

ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ መሰል ጽሑፍ ቢያሰፍር፤ ትዊተር ጽሑፉን ያጠፋው ነበር። የተጠቃሚው ገጽም ይሰረዝ ነበር።

በትዊተር ሕግ መሠረት፤ የትዊተር ተጠቃሚዎች ለትራምፕ ጽሑፍ መልስ መስጠት፣ መልሰው ትዊት ማድረግ ወይም ጽሑፉን መውደዳቸውን ለመግለጽ ‘ላይክ’ ማድረግ አይችሉም።

ጽሑፉን መልሰው ለሌሎች ማጋራት ከፈለጉ አብሮት አስተያየት ይኖራል።

“ይህ ትዊት ግጭትን የሚያበረታተቱ ጽሑፎችን ለመግታት ያወጣነውን ፖሊሲ ይጻረራል። የጽሑፉን ታሪካዊ ዳራ ሲታይ ከግጨት ጋር የተያያዘና ግጭት ሊቀሰቅስ የሚችልም ነው” ሲል ትዊተር አቋሙን ገልጿል።

ትዊተር የጽሑፉ ታሪካዎ ዳራ ያለው፤ የማያሚ የፖሊስ ኃላፊ ዋልተር ኸርድሊ እአአ በ1967 “ማውደም ከተጀመረ መተኮስ ይጀመራል” ሲሉ የተናገሩትን በማጣቀስ ነው።

የፖሊስ ኃላፊው ይህን የተናገሩት ጥቁሮች በሚኖሩበት ሰፈር ፖሊሶች ከፍተኛ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያደርገውን ፖሊሲያቸውን ደግፈው ነበር።

የፖሊስ ኃላፊው የማያሚ ፖሊሶች በጥቁሮች ሰፈር መሣሪያና ውሾች ይዘው እንዲዘዋወሩ የሚያበረታታ ፖሊሲ ነበራቸው። ይህም በአካባቢው ከስምንት ወራት በኋላ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል።

ትዊተር “ሰዎች ለግጭት እንዳይነሳሱ ስንል እርምጃውን ወስደናል። ትዊቱን ግን አላጠፋነውም። ምክንያቱም አሁን እየተከናወኑ ካሉ ነገሮች አንጻር ሕዝቡ ትዊቱን እንዲመለከት እንሻለን” ሲል መልዕክት አስተላልፏል።

ትዊተር የትራምፕ ጽሑፍ ላይ ማስጠንቀቂያ ካስቀመጠ በኋላ ፕሬዘዳንቱ ትዊተር ሪፐብሊካኖች ላይ አነጣጥሯል ሲሉ ወንጅለዋል። “የቻይና እና የግራ ዘመሙ ዴሞክራቲክ ፓርቲን ውሸትና ፕሮፓጋንዳ በተመለከተ ትዊተር እርምጃ አልወሰደም” ብለዋል።

ትዊተር ማስጠንቀቂያውን ከማውጣቱ ከአንድ ቀን በፊት ለማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሰጠውን ከለላ የሚያነሳ ውሳኔ ማስተላለፋቸውንም ፕሬዘዳንቱ አስታውቀዋል።

ትዊተር ለመጀመሪያ ጊዜ የትራምን ትዊት “እውነታውን ያጣሩ” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር ማውጣቱን ተከትሎ፤ ፕሬዘዳንቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ነፃ ንግግርን እያገዱ ነው ብለው ተቋሞቹን ለመዝጋት ሲያስፈራሩ ነበር።

በእርግጥ ትራምፕ ያስተላለፉት ውሳኔ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አሁን ጫና አያሳርፍም። በጊዜ ሂደት ግን አንዳንድ ለውጦች ሊያስከትል ይችላል።