ዶናልድ ትራምፕ ለዶ/ር ቴድሮስ የ30 ቀን ጊዜ ገደብ ሰጡ

ዶናልድ ትራምፕ ለዶ/ር ቴድሮስ የ30 ቀን ጊዜ ገደብ ሰጡ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የ30 ቀን ማስጠንቀቂያ ሰጡ።

ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ቴዎድሮስን በሰላሳ ቀናት በድርጅታቸው ውስጥ "መሰረታዊ ለውጥ" እንዲያመጡ ያሳሰቡ ሲሆን አለበለዚያ ግን አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ለድርጅቱ የምታደርገውን ድጋፍ ታቋርጣለች ሲሉ ለዶ/ር ቴድሮስ በጻፉት ደብዳቤ አስጠንቅዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለዶ/ር ቴዎድሮስ የጻፉትን ደብዳቤ በትዊተር ገፃቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት የሚጠበቅበትን በሚገባ ስላለመወጣቱ ሲናገሩ ቫይረሱ ከቻይናዋ ዉሃን በተነሳበት ወቅት "በተደጋጋሚ ስለ ቫይረሱ ስርጭት አስመልክቶ ይቀርቡ የነበሩ ተጨባጭ መረጃዎችን ችላ ብሏል" ሲሉ ወቅሰዋል።

አክለውም የዓለም ጤና ድርጅት በተደጋጋሚ ቻይናን "ሲያንቆለጳጵስ" ነበር በማለት የዓለም ጤና ድርጅት "መሰረታዊ የሆነ ማሻሻያ ካላደረገ" በማለት በጊዜያዊነት ያቋረጡትን የአሜሪካ ድጋፍ በቋሚነት ለማድረግና "አባልነታችንንም እናስብበታለን" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅትን መወንጀል ብቻ ሳይሆን ድርጅቱ "የቻይና አሻንጉሊት" ነው ሲሉም ጠንከር ያለ ወቀሳም ሰንዝረዋል።

ይህ አስተያየታቸው የተሰማው ድርጅቱ በወረርሽኙ ላይ የሁለት ቀናት ጉባዔ እያካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

አክለውም የዓለም ጤና ድርጅት "የተለያዩ መጥፎ ምክሮችን ሲሰጠን ነበር" ካሉ በኋላ ምክሮቹ "በጣም ስህተት የነበሩና ሁሌም ወደ ቻይና ያደሉ ነበሩ" ብለዋል።

በጉባዔው ፕሬዝዳንቱ ራሳቸው ያልተገኙ ሲሆን የጤና ሚኒስትራቸው ግን ስብሰባውን በቪዲዮ ተካፍለዋል።

ሚኒስትሩ ድርጅቱ ወረርሽኙን የያዘበት የተሳሳተ መንገድ "ለበርካቶች ህይወት መቀጠፍ" ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ትራምፕ በአገራቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሰጡት ምላሽ የሚኮነኑ ሲሆን እርሳቸው ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅትን ስለወረርሽኙ የዓለም ሕዝብን ቀድሞ አላሳወቀም፤ በቂ አላደረገም እንዲሁም በቻይና ላይ ከበቂ በላይ እምንት አለው በማለት ይተቹታል።

አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት የምታደርገውን ድጋፍ ማቋረጧ ይታወሳል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለሁለት ቀናት እያካሄደ ያለው አመታዊ ጉባዔውን 194 አባል አገራት የሚሳተፉበት ሲሆን የድርጅቱን ስራዎችም መለስ ብለው ይገመግማሉ ተብሏል።

ዓለምን የናጣት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ልዕለ ኃያላኑ አሜሪካና ቻይናን ጠብ ያለሽ በዳቦ እያሰኘ ነው። የዶ/ር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት እንዲህ በዓለም ፖለቲካ ትንቅንቅ መሃል እገኛለሁ ብሎ ያሰበ አይመስልም። አሜሪካን ቻይናን ትከሳለች፤ ቻይና ደግሞ ያለስሜ ስም አትስጭኝ ትላለች።

የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ቫይረሱ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚለው በገለልተኛ ወገን ይጣራ ይላል። የትኛው እንሰሳ ኮሮናቫይረስን ወደ ሰው ልጅ አስተላለፈ የሚለው አንቀፅ ላይ የአውሮፓ ሕብረት የቻይናን ስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

300 ሺህ ሕዝብ በጥቂት ወራት የቀጠፈው ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ቻይና ውስጥ ነው።

ሌሎች ደግሞ ገለልተኛ የሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አጣሪ ቻይና ገብቶ መነሾውን ቆፍሮ ያውጣ ይላሉ። እስካሁን ድረስ ባለው ማጣራት ቻይና ገለልተኛ ወገኖች እንደልባቸው እንዲሆኑ አልፈቀደችም። አሜሪካና አውስትራሊያ ደግሞ እንዴት ተኩኖ እያሉ ነው። ቻይና አቋሟን ትቀይራለች ብሎ መጠበቅ የዋህነት ሳይሆን አይቀርም።

ጉባዔውን 'መርቀው' የከፈቱት የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂፐንፒንግ 'ሃገሬ በሽታውን ግልፅ በሆነ መንገድ ነው የተቆጣጠረችው' ይላሉ። 'አይሆንም እናጣራ የምትሉ ከሆነ ደግሞ መጀመሪያ በሽታውን በቁጥጥር ሥር እናውለው' ባይ ናቸው።