እስራኤል የመጀመሪያዋን ቤተ እስራኤላዊት በሚኒስትርነት ሾመች

እስራኤል የመጀመሪያዋን ቤተ እስራኤላዊት በሚኒስትርነት ሾመች

በምስጢራዊ የሞሳድ ተልዕኮ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ከሄዱ ዜጎች መካከል ለዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ በመብቃት የመጀመሪያዋ ትሆናለች።

ቤተ እስራኤላዊቷ ኒና ታማኖ-ሻታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር የአንድነት መንግሥት እየመሰረቱ ያሉትና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በሚረከቡት ቤኒ ጋንትዝ ነው ለሚኒስትርነት የታጨችው።

አዲሱ የእስራኤል የአንድነት መንግሥት ምስረታ በሚኒስትሮች ሹመት ሳቢያ የዘገየ ሲሆን እሁድ ዕለት ቃለ መሐላ ፈጽሞ ሥልጣኑን እንደሚረከብ ተነግሯል።

የቀጣዩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ ፓርቲ አባል የሆነችው ቤተ እስራኤላዊቷ ኒና ታማኖ-ሻታ የአገሪቱ መንግሥት ውስጥ የስደተኞች ሚኒስተር ሆና ተሹማለች።

ወታደራዊው የኢትዮጵያ መንግሥት ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በ1976 እና 77 እጅግ አስደናቂ ነው በተባለው የዘመቻ ሙሴ በእስራኤል የስላላ ድርጅት ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲደረግ የአሁኗ ተሿሚ ሚኒስትር የሦስት ዓመት ህጻን ሆና ነው ወደ እስራኤል የሄደችው።

በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሄዱ ቤተ እስራኤላዊያን መድልዎ እንደሚፈጸምባቸው በተደጋጋሚ አቤቱታ ያቀርባሉ። በዚህም ሳቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወደ ጎዳናዎች ለበርካታ ጊዜ ወጥተዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ ቤተእስራኤላዊያን 140 ሺህ የሚደርስ ቁጥር ያለቸው ሲሆን ከመካከላቸውም አብዛኞቹ ሥራ አጥ በመሆናቸው በአገሪቱ ውስጥ በድህነት ከሚኖሩት መካከል ይመደባሉ።

ነገር ግን እስራኤል ውስጥ ተወልደው ያደጉ በርካታ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤላዊያን በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ውስጥ፣ በዳኝነት መስክና በፖለቲካ ውስጠይ ተሳትፈው ስኬታማ ለመሆን ችለዋል።

ከሰላሳ ዓመታት በፊት እስራኤል በምስጢር ቤተ እስራኤላዊያንን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ዘርግታው በነበረው ዕቅድ 16 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን አይሁዶች ከሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል ተነስተው ወደ ሱዳን በእግራቸው የገቡ ሲሆን ከዚያም በአውሮፕላን ወደ እስራኤል ተወስደዋል።

በወቅቱ ከኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድ ለመውጣት አስቸጋሪ ስለነበረ የእግር ጉዟቸውን ያደረጉት በምስጢር ሲሆን ሱዳን ውስጥ ወደሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ከመድረሳቸው በፊት ከመካከላቸው 1,500 የሚሆኑት በመንገድ ላይ ህይወታቸው አልፏል።

ከአረቡ ዓለም ጋር በወቅቱ ፍጥጫ ላይ የነበረችው እስራኤል የሙስሊሞች አገር የሆነችው ሱዳንን ነበር በምስጢር ቤተ እስራኤላዊያኑን ለማስወጣት እንደመተላለፊያ የተጠቀመችው።

ኢትዮጵያዊያኑን አይሁዶች በድብቅ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ከዚያም ወደ እስራኤል የማጓጓዙ የመጀመሪያዎቹ ተልዕኮዎች የተከናወኑት በእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ አማካይነት ነበር።