የህንድ ሆስፒታል ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው እናቶች ከ100 በላይ ህጻናትን አዋለደ

የህንድ ሆስፒታል ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው እናቶች ከ100 በላይ ህጻናትን አዋለደ

በህንዷ ሙምባይ ከተማ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ከ100 በላይ የሚሆኑ ጤናማ ህጻናት በኮሮናቫይረስ ከተያዙ እናቶች ማዋለዱን አስታወቀ።

ሆስፒታሉ ባለፈው የሚያዝያ ወር ቫይረሱ ካለባቸው እናቶች ካዋለዳቸው 115 ህጻናት ውስጥ መጀመሪያ ላይ ሦስቱ ቫይረሱ እንደለባቸው የተነገሪ ቢሆንም በድጋሚ በተደረገ ምርመራ ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ዶክተሮች ተናግረዋል።

ለመውለድ ወደ ሆስፒታሉ ከመጡት በበሽታው ከተያዙ እናቶች መካከል ሁለቱ በሆስፒታሉ ውስጥ የሞቱ ሲሆን አንዷ ልጇን ከመገላገሏ በፊት ነበር ህይወቷ ያለፈው።

የህንድ የገንዘብና የመዝናኛ ከተማ በሆነችው ሙምባይ እስካሁን ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎቿ ላይ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን ከ730 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

በሎክማኒያ ቲልካ በተባለው አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ የኮሮናቫይረስ ካለባቸው እናቶች ከተወለዱት ህጻናት ከግማሽ የሚበልጡት በቀዶ ህክምና የተወለዱ ሲሆን የተቀሩት ግን በተፈጥሯዊ መንገድ መውለዳቸውን የሐኪም ቤቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል።

ከተወለዱት ህጻናት መካከል 56ቱ ወንዶች ሲሆኑ 59ኙ ድግሞ ሴቶች ናቸው። በሽታው ከተገኘባቸው እናቶች መካከል ሃያ ሁለቱ ወደ ሌላ ሆስፒታል የተላኩ ሲሆን በቫይረሱ እንዴት ሊያዙ እንደቻሉ አልታወቀም።

"ቫይረሱ ከተገኘባቸው ወላዶቹ መካከል አብዛኞቹ የበሽታውን ምንም አይነት ምልክት ያላሳዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው ትኩሳትና ትንፋሽ ማጠር የታየባቸው ሲሉ ሐኪሞቹ ተናግረዋል።