ኮሮናቫይረስ፡ የወባ መድኃኒት ምን ያህል ኮሮናቫይረስን ለማከም ይችላል?

ኮሮናቫይረስ፡ የወባ መድኃኒት ምን ያህል ኮሮናቫይረስን ለማከም ይችላል?

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለወባ ህመምተኞች ማከሚያ የተሠሩ መድኃኒቶች ለኮቪድ-19 ህክምና ይውላሉ ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ የበርካቶች መነጋገሪያ ከሆነ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

በእርግጥ እንደ ክሎሮክዊን ያሉ መድኃኒቶች ኮቪድ-19ኝን ያክሙ እንደሆነ ገና ምርምር እየተደረገባቸው ነው።

ሆኖም አንዳንዶች ይህን መድኃኒት ራሳቸውን ለማከም መሞከራቸው የዓለም ጤና ድርጅትን አስግቷል።

ከአሜሪካ የክትባት ምርምር መሪነታቸው የተነሱት ዶክተር ሪክ ብራይት እንዳሉት፤ ትራምፕ በዚህ መድኃኒት ላይ ማተኮራቸው ብዙ ሳይንቲስቶችን አወዛግቧል።

መድኃኒቱ በስፋት እየተነገረለት ስለሆነም በዓለም ገበያ ተፈላጊነቱ ጨምሯል።

ስለመድኃኒ ምን እናውቃለን?

ትራምፕ በሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ሀይድሮክሲክሎሮክዊንን ደጋግመው ያነሳሉ። እንዲያውም “ብትወሰዱ ምን ይጎልባችኋል?” ብለዋል።

የብራዚሉ ፕሬዘዳንት ዣይር ቦልሶናሮ “ሀይድሮክሲክሎሮክዊን በየቦታው እየሠራ ነው” ቢሉም፤ ፌስቡክ የሐሰተኛ መረጃ ደንብን የተላለፈ ነው ብሎ መልዕክቱን አጥፍቶታል።

ትራምፕ መጋቢት ላይ ስለመድኃኒቱ መናገራቸውን ተከትሎ፤ የሀይድሮክሲክሎሮክዊን እንዲሁም የክሎሮክዊን ፍላጎት ጨምሮ ነበር።

ክሎሮክዊን የያዙ እንክብሎች ወባን ያክማሉ። ትኩሳት የሚቀንሱ ሲሆን፤ ኮቪድ-19ኝ የሚያስከትለውን ቫይረስ ሊያክሙ ያስችላሉ የሚል ተስፋ አለ።

አሁን ላይ ይህ እውነት ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ የለም። ሰዎች ላይ የኩላሊትና ሳምባ ጉዳትን ጨምሮ ሌሎችም የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ እተባለ ነው።

የወባ መድኃኒት ለኮቪድ-19 የሚውል ስለመሆኑ ሪፖርት የሠሩት የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው ተመራማሪ ኮሜ ጊንጊኔ እንደሚሉት፤ መድኃኒቱ ውጤታማ መሆኑን ለማረጋገጥ ሰፊ የሙከራ ሂደቶችን ማለፍ አለባቸው።

በዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ስፔን እና ቻይና ከ20 በላይ ሙከራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

በአሜሪካ በክሎሮክዊን፣ በሀይድሮክሲክሎሮክዊን እንዲሁም አዚትሮሚሲን በተባለ ፀረ ተህዋስን (አንቲባዮቲክ) በማዋሃድ ኮቪድ-19ን ለማከም ሙከራ እየተደረገ ነው።

መድኃኒቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የፈቀዱት የትኞቹ አገራት ናቸው?

መጋቢት መጨረሻ ላይ የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ተቋም መድኃኒቶቹ ለተወሰኑ ሰዎች ህክምና እንዲውሉ ‘የአስቸኳይ ጊዜ ፍቃድ’ ሰጥተዋል።

ይህ ማለት ግን መድኃኒቶቹ ይሠራሉ ማለት እንዳልሆነ ግን ተቋሙ ገልጿል። ለተወሰኑ የኮቪድ-19 ምርመራዎች ሆስፒታሎች መድኃኒቶቹን ማዘዝ ይችላሉ።

በአንዳንድ ህሙማን የልብ ምት ችግር መታየቱን ተከትሎ፤ ሚያዝያ ላይ ተቋሙ መድኃኒቶቹ አደገኛ እንደሆኑ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ጀርምን አየሚገኝ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ 30 ሚሊዮን ሀይድሮክሲክሎሮክዊን ለአሜሪካ ብሔራዊ የመድኃኒት ክምችት መለገሱም ተገልጿል።

ፈረንሳይ ለኮቪድ-19 ታማሚዎች መድኃኒቱ እንዲሰት ብትፈቅድም የህክምና ባለሙያዎች ተቆጣጣሪ ተቋም ስለ መድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የሕንድ መንግሥት መድኃኒቱ ጥቅም ላይ እንዲውል መክሯል። የአገሪቱ የምርምር ተቋም ግን መድኃኒቱ ገና በሙከራ ላይ ያለ እንደመሆኑ ለአስቸኳይ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ መዋል አለበት ብሏል።

በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መድኃኒቱ ጥቅም ላይ እንዲውል የፈቀዱ ሲሆን፤ ሙከራ ላይ የሚገኙም አሉ። ከእነዚህ መካከል በሀይድሮክሲክሎሮክዊን ኮቪድ-19ኝን ካከሙ አገሮች አንዷ መሆኗን የምትገልጸው ባህሬን ትገኝበታለች። ሞሮኮ፣ አልጄሪያና ቱኒዝያም ይቀሳሉ።

በቂ ሀይድሮክሲክሎሮክዊን አለ?

መድኃኒቱ ኮቪድ-19ኝን ለማከም ሊውል ይችላል ከተባለ በኋላ የበርታ አገራት ፍላጎት ጨምሯል።

በተለይም በታዳጊ አገራት ክሎሮክዊን እና መሰል መድኃኒቶች በየፋርማሲው ይገኛሉ። በእርግጥ ወባ እየጠነከረ ስለመጣ የመድኃኒቱ ውጤታማነት እየቀነሰ ነው።

ዮርዳኖስ ሰዎች ሀይድሮክሲክሎሮክዊን ገዝተው እንዳያከማቹ በሚል የመድኃኒቱን ሽያጭ አግዳለች። ኩዌት ደግሞ በሆስፒታሎችና የጤና ማዕከሎች ብቻ እንዲሸጥ ወስናለች።

ከአፍሪካ አገራት ደግሞ ኬንያ መድኃኒቱ ያለ ሐኪም ማዘዣ ለማንም እዳይሸጥ አግዳለች።

ሕንድ መድኃኒቱን በዋነኛነት ታመርት ነበር። በአንድ ወቅት ግን ለውጪ ገበያ እንዳይቀርብ ማዕቀብ ጥላ የነበረ ቢሆንም፤ ትራምፕ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲን በግል ካነጋገሩ በኋላ ማዕቀቡ ተነስቷል።

መድኃኒቱን ያለ ትዕዛዝ መውሰድ ለአደጋ ያጋልጣል

በናይጄሪያ ክሎሮክዊን ያላቸው እንክብሎች ወባን ለማከም ይውላሉ። እአአ 2005 ላይ የመድኃኒቱ ውጤታማነት በመቀነሱ ታግዶ ነበር።

ክሎሮክዊንን ለኮቪድ-19 ስለመጠቀም ቻይና ውስጥ የተሠራ ጥናት በናይጄሪያዋ ሌጎስ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ሰዎች መድኃኒቱን ማጠራቀምም ጀምረዋል።

ትራምፕ በሽታውን ለማከም ይውላል ሲሉ ደግሞ የመድኃኒቱ ፍላጎት በእጥፍ ጨምሯል። ከመድኃኒት መደብሮች ተሽጦ ለማለቅም ጊዜ አልወሰደበትም።

የናይጄሪያ የበሽታ ቁጥጥር ተቋም በበኩሉ ሰዎች መድኃኒቱን እንዳይወስዱ አስጠንቅቋል።

በሌላ በኩል የናይጄሪያዋ ባውቺ ግዛት አገረ ገዢ ባላ ሞሐመድ፤ መድኃኒቱን ከወሰዱ በኋላ ሌሎች ሰዎችም እንዲጠቀሙበት መክረዋል።

የሌጎስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት፤ መድኃኒቱን ከመጠን በላይ ወስደው ሰውነታቸው የተመረዘ ሰዎች በርካታ ናቸው።