የምጡቅ አዕምሮን የታደለው ታዳጊ ፈጠራ ባለቤት

የምጡቅ አዕምሮን የታደለው ታዳጊ ፈጠራ ባለቤት

ሳይንሳዊ ግኝት የላቀ ክህሎትና ምጡቅ አዕምሮ በመጠቀም በሀሳብ የነበረ ንድፍ ወደ ተግባር የመለወጥ ችሎታ የሚጠይቅ ነው። እሳቤን ወደ ተግባር በመለወጥ ውጤት ለማምጣት በብዙ ጥረትና ልፋት ውስጥ ማለፋ ያስፈልጋል ።

ሳይንሳዊ ግኝት የላቀ ክህሎትና ምጡቅ አዕምሮ በመጠቀም በሀሳብ የነበረ ንድፍ ወደ ተግባር የመለወጥ ችሎታ የሚጠይቅ ነው። እሳቤን ወደ ተግባር በመለወጥ ውጤት ለማምጣት በብዙ ጥረትና ልፋት ውስጥ ማለፋ ያስፈልጋል ። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተጠበው አእምሮአቸው ያፈለቀውን ንድፈ ሀሳብ ተግባር ላይ ለማዋል በመትጋት፤ ስራቸው እውን ሆኖ ማየት የዘወትር ህልማቸው ነው።

የፈጠራ ባለሙያዎች የማህበረሰቡን ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ፤ ማህበራዊ ፋይዳቸው የጎላ ፈጠራዎች፤ በተለይ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮአዊ ክስተቶች ወቅት ፈጣን መፍትሔ በመፈለግ ቀዳሚ ሆነው በመገኘት መላዎች ይዘይዳሉ።
ዛሬ ላይ እያየን ያለነው የፈጠራ ባለሙያዎች ፤ ገና በለጋነት እድሜ ለነገ የሀገራችን የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ የሆኑ ባለብሩህ አእምሮ ባለቤቶች ናቸው ። ከጅምራቸው ነገ አሻግሮ የሚያሳዩ፤ ያላቸው ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ከእድሜያቸው በላይ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች ሰርተው ፤ ለነገ ያላቸውን ተሰፋ ካሳዩን መካካል ተማሪ ኑሩ ጀማል አንዱ ነው ።

በሀገራችን የተከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ ለመከላከል ለስድስት ወራት ባደረገው ጥረት ለኬሚካል መርጫ አገልግሎት የሚውል ድሮውን የሰራ ባለሙያ ነው።
ኑሩ ጀማል የኮምቦልቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው ። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ነገሮችን በመነካካት በሚያገኘው ውጤት የፈጠራ ዝንባሌ እንዳደረበት ይናገራል። በፈጠራ ስራው ይበልጥ እንዲተጋ ቤተሰቦቹ የሀሳብ ና የሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ከፍ ያለ ሚና አላቸው። በተለይ
የፊዚክስ መምህሩ ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል።

የፈጠራ ስራው ምንነት
የታዳጊው ወጣት ኑሩ ጀማል የፈጠራ ስራ፤ በአካባቢው ከሚገኙ የወዳደቁ ቁሳቁሶች የተሰራ ሲሆን፤ የአንበጣ ወረርሽኝ ለመከላከል አገልግሎት የሚውል ኬሚካል መርጨት የሚያስችል ድሮውን ነው። ድሮውኑ ከ2ሊትር እስከ 3ሊትር ኬሚካል መሽከም የሚችል፣ በጸሀይ ብርሀን የሚሰራና ቻርጅ የሚደረግ ነው። የሚጮኸ ስፒከር የተገጠመለት እስከ 2 ኪሎ ሜትር ድረስ መጓዝ የሚችል ነው።

ተማሪ ኑሩ፤ እስካአሁን ከ28 በላይ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች አሉት። ከስራዎቹም መካከልም የትራፊክ አደጋን መከላከል የሚያስችል የመብራት ሴንሰር ወይም ሁለት ከተለያዩ አቅጣጫ የሚመጡ መኪናዎች በጠመዝማዛ መንገድ አንድ ላይ በሚገናኙበት ወቅት እንዳይጋጩ ሴንሰር በማድረግ ከፊት ሌላ መኪና መኖሩን እንዲያውቅ የሚያደርግ ፈጠራ፤ በጸሀይ ብርሀን የሚሰራ መብራት፤ እጽዋቶች ውሃ ሲጠማቸው አውቆ ሴንስ የሚያደርግ መሳሪያ፤ በጸሀይ ብርሀን የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ሞተር ፤ የኤፍ ኤም ማሰራጫ ትራንስሚተር የሚጠቀሱ ናቸው።

የፈጠራ ስራው ጠቀሜታ
ሰው አልባ ድሮውኑ አንበጣ ለመቆጣጣር የሚያስችል ኬሚካል የሚረጭ ሲሆን አንበጣ ባለበት ቦታ ሲደርስ የሚጮህ ድምፅ እያሰማ አንበጦችን የማባረር አቅም አለው ። የፈጠራ ስራ ሶፍት ዌር የተገጠመለት በመሆኑ፤ ማንኛውም ሰው በተገጠመለት የሪሞት መቆጣጠሪያ ሊጠቀምበት የሚችለው ነው።

የፈጠራ ስራው አሁን ያለበት ደረጃ
የፈጠራ ስራው፤ አሁን ላይ ኮምቦልቻ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ስራን መስራት የቻለ ነው። አንበጣ የተከሰተበት ቦታ ላይ ቢወሰድ ተግባራዊ መሆን የሚችል ነው።
ተማሪ ኑሩ፤ ድሮውኑ በማሻሻል በመስመር መዝራት እንዲችል ለማድረግ እየሰራ ነው። በሚፈ ለግበት ቦታ በተገጠመለት የሪሞት መቆጣጠሪያ በመታገዝ ሰብልን የመዝራት ስራ ያከናውናል። በዲጅታል መረጃ በመታገዝ ኬሚካል እንዲረጭና በመስመር እንዲዘሩ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራል።

የፈጠራ ስራውን በስፋት በትምህርት ቤቱ ቤተሙከራዎችና በቤት ውስጥ እየስራ እንደሚገኝ የሚገልጸው ኑሩ፤ የፈጠራ ስራዎቹን ጥቅም ላይ ለማዋል ትብብር ድጋፍ ከሚያደርግለት አካላት ቢያገኙ ምርቱን ለማምረት እንደሚቻል ይናገራል። የፈጠራ ባለቤትነት መብት ለማግኘትም አእምሮዊ ንብረት ለማስመዝገብ ሂደት ላይ እንደሆነ አስታውቋል ።
በፈጠራው ስራው ያስገኘው እውቅናና ሽልማት፡-

ኑሩ በሀገር፣ በክልልና በዞን ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶች አግኝቷል። በ2008 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ሽልማት የእውቅና ሰርተፍኬትና የነሃስ ሜዳሊያ ሽልማት አግኝተዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት በተዘጋጀ የወጣቶችና የታዳጊዎች ውድድር፤ ቡሉሞን አፍሪካ በተካሄደ የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ የፈጠራ ስራዎቹን በማቅረብ እውቅናና ሽልማቶች አግኝቷል።

ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት እቅዶች
አብዛኛውን ጊዜ ለስራው የሚያገለግሉት ቁሳቁሶች ለማግኘት እንደሚቸገር የሚገልጸው ኑሩ፤ በግብርና ዘርፍ እና በትራፊክ አደጋ ዙሪያ ያሉ ችግሮች የሚቀርፍ ቴክኖሎጂ በመስራት ህብረተሰቡ ለማገዝ ይፈልጋል።
ታዳጊው በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራዎችን በመስራት የራሱ አሻራ በማስቀመጥ ህልሙን እውን የማድረግ ፤ ወደፊትም በሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ላይ በመሳተፍ የፈጠራ ስራዎችን በማፍለቅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስን ያልማል። የፈጠራ ባለሙያ ተማሪ እንደመሆኑ መጠን ለምርምርና ለፈጠራ የሚሆን አቅም የለውም።

በመሆኑም ፤ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግልን አካል ያስፈልገዋል። ለወደፊት የተሻለ ስራዎችን እንዲሰራ የሚያበረታታና ድጋፍ የሚያደረግለት አካላት እንደሚፈልግና ትብብር እንዲደረግለት ጥሪ አቅርቧል ።
የታዳጊው የፈጠራ ውጤት ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ፤ ለግብርና ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል ይታመናል። የነገ የሀገሪቱ ተስፋ ሊሆኑ የሚችል ነውና ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባል እንላለን።