ሳሙናን በኪስ ያስያዘ የፈጠራ ሥራ

ሳሙናን በኪስ ያስያዘ የፈጠራ ሥራ

የ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ዓለምን ውጥረት ውስጥ በመክተት የብዙዎች ስጋት መሆኑ እንደቀጠለ ነው፡፡

የ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ዓለምን ውጥረት ውስጥ በመክተት የብዙዎች ስጋት መሆኑ እንደቀጠለ ነው፡፡ በዓለም ላይ በየጊዜው ለሚከሰቱ በሽታዎች መፍትሔ የሚሆን መላ የሚዘይዱ ሳይንቲስቶችን ሳይቀር ፈተና ውስጥ ከቷል፡፡ ሳይንቲስቶቹ ፈዋሽ መደኃኒትም ሆነ ክትባት ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረትና ውጤት እስከሚያገኙ ድረስም ይቀጥላል፡፡ ሳይንሳዊ ምርምር አንዳች መላ ፍለጋ አድካሚና ብዙ ልፋት የሚጠይቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ያሉ ተመራማሪዎች ቫይረሱ ቻይና ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ወደ ተግባር ተሰማርተው የራሳቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ ባለሙያዎች ያላቸው እውቀት በመጠቀም ፈጣን መፍትሔ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት አበረታች ነው፡፡ በዚህም ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎችም ሆኑ ሌሎች ተሳታፊ ሆነዋል። ለመከላከል የሚረዱ መፍትሔ ይሆናል ብለው ያሰቡትን ሥራዎች ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የራሳቸው የፈጠራ ሥራ ካበረከቱት በርካታ ተመራማሪዎች መካከል ኢንጂነር ናሆም መኮንንና ኢንጂነር የኋላሸት ንጉሴ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች ኮቪዲ 19 ቫይረስን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ኅብረተሰቡን ከቫይረሱ ይታደጋል ያሉትን የፈጠራ ሥራ ሰርተዋል፡፡
ወጣቶቹ ባላቸው እውቀት ተጠቅመው ለመከላከል የሚረዳ ከሰዎች እጅ ንክኪ ነፃ የሚያደርግ በኪስ የሚያዝ ሳሙና መስራት ችለዋል፡፡ ለወጣቶቹ የፈጠራ ሀሳብ መነሻ ሆኖ ሀሳባቸው እውን እንዲሆን ያደርገው ኮቪዲ 19 ቫይረስ ቢሆንም የእጅ መታጠብ ባህላችንንና የንክኪ ጉዳይ የሁል ጊዜ ትዝብታቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ መጀመሪያ ውጥናቸው የነበረውን ፈሳሽ ሳሙና መስራት ሀሳብ በመግታት ከእጅ ንክኪ ነፃ የሚያደርገው አዲስ ፈጠራ ለመስራት መቻላቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ይህንን ሀሳብ መነሻ በማድረግ የሰሩት ውጤታማ የፈጠራ ሥራ ለኮሮና ቫይረስ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል እንዲሆን አድርገው በመስራት መላ መዘየድ ችለዋል፡፡ የኢንጂነር ናሆም መኮንንና የኢንጂነር የኋላሸት ንጉሴ የፈጠራ ሥራ፤ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሚያደርግ በኪስ የሚያዝ ሳሙና ነው፡፡ ሳሙናው የተሰራው የጨርቅነት ባህሪ ካለው ቁሳቁስና ኬሚካል ሲሆን፤ አንዱ እሽግ አስራ አምስት ዘለላዎችን የሚይዝ ነው።
የፈጠራ ሥራው ጠቀሜታ
የፈጠራ ሥራው፤ በርከት ያሉ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው፡፡ ሳሙናው በቀላሉ በኪስ የሚያዝ ስለሆነ እንቅስቃሴ ስናደርግ ይዘን መጓዝ እንችላለን። የእጅ ንክኪን በማስቀረት እጅን በደንብ ለማሸት ያገለግላል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣው የእጅ አስተጣጠብ ሂደት ተከትሎ እንዲታጠቡ ይረዳል። የሳሙናውን አንዷን ዘለላ ከተጠቀምን በኋላ ኬሚካሉ ስለሚለቅ ወይም የሳሙናነት ባህሪው ስለሚለቅ ቧንቧው ከእጃችን ጋር ንክኪ እንዳይኖረው ለማድረግ ቧንቧውን ተጭነን ለመዝጋት ይጠቅመናል፡፡ ተጠቅመን ከጨረስን በኋላ አገልግሎት ስለማይሰጥ የሚጣል ይሆናል፡፡ በመሆኑም የፈጠራ ሥራው እጅ መታጠብ የሁልጊዜ ልምድ መደረግ ያለበት፤ የራስን ሳሙና በኪስ ይዞ በመሄድ ከብዙ በሽታዎች ለመከላከል ይጠቅማል፡፡
የፈጠራ ሥራው አሁን ያለበት ደረጃ
የወጣቶቹን የፈጠራ ሥራ እነሱን ጨምሮ በአካባቢያቸው የሚገኙ በርካታ ሰዎች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ከተጠቃሚዎቹ ያገኙት ምላሽ አበረታች መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የፈጠራ ሥራው የእጅ ንክኪን በማስወገድ የኮሮና መተላለፊያ መንገድ በመቀነስ በምንታጠብበት ወቅት ከንክኪ ነፃ እንድንሆን ታስቦ የተሰራ ሥራ ነው፡፡ ይህንን በኅብረተሰቡ ዘንድ በማድረስ ተጠቃሚ ለማድረግ በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ኮቪድ 19 ቫይረሱን ማስቀረት ባይቻል መከላከል ይቻላል፡፡ እጅን በሳሙና መታጠብ በሽታው ሲጠፋም የሚያቆም ነገር አይደለም፤ ለወደፊቱ እጅ መታጠብ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ስለሚያስፈልግ ለሁልጊዜ የሚያገለግል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የፈጠራ ሥራው በስፋት በማምረት ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታ እያመቻቹ ነው፡፡
በተጨማሪም እነሱን ጨምሮ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር የሚችልም ሥራ ነው፡፡ አሁን ላይ ሳሙናውን የሚያመርቱበት ቁሳቁሶች ከውጭ ሀገር የሚገቡ በሀገር ውስጥ ገበያ የሚገኙ ናቸው፡፡ የገንዘብና የመስሪያ ቦታ ሥራዎች ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው አካላት ቢያገኙ ምርቱን በስፋት ለመጀመር እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ለማግኘትም አእምሯዊ ንብረት ለማስመዝገብ ሂደት ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት እቅዶች
የወጣቶቹ የፈጠራ ሥራ፤ ጊዜ የማይሰጠውን የኮሮና ቫይረስ በአፋጣኝ ለመከላከል ጠቃሚ ነው፡፡ የፈጠራ ሥራው ከፍተኛ የፋይናንስና የሞራል ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን ይናገራሉ። የፈጠራ ባለሙያዎቹ ህልም ኮሮና ቫይረስ በመከላከል የሚረዱ የተሻሉ ሥራዎች ለኅብረተሰቡ በቶሎ ለማድረስ ነው፡፡ ለወደፊት ሥራውን ለማስቀጠል የሚያበረታቱና ድጋፍ የሚያደርጉላቸው አካላትን ትብብርም ይሻሉ፡፡ ወጣቶቹ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻቸውን በመወጣት ረገድ እያደረጉ ያለው አስተዋፅኦ ጉልህ ነውና፤ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ ቢደረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለት እንወዳለን፡፡