የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከኦሊምፒክ ቀድሞ ይካሄዳል

የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከኦሊምፒክ ቀድሞ ይካሄዳል

የኮሮና ቫይረስ(ኮቪድ 19) በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት መሰራጨቱን ተከትሎ የሁሉም ዓለም አቀፍ የስፖርት መርሃግብሮች ዝብርቅርቅ መውጣቱ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ታላላቅ የስፖርት መርሃግብሮችን ዳግም መከለስ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በዚህም መሰረት ክለሳ የተደረገባቸው የተለያዩ መርሃግብሮች ውዝግብ ሲያስነሱ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡

ከተያዘለት መርሃግብር እንዲራዘም የተደረገው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ2021 እንዲካሄድ ከተራዘመው የቶኪዮ ኦሊምፒክ አስቀድሞ እንዲካሄድ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ውሳኔ ላይ መድረሱን ከሁለት ቀናት በፊት አሳውቋል፡፡ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሐማድ ካልካባ በአልጄሪያ የሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ እንደሚካሄድ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ካልካባ የውድድሩ አዘጋጅ አገርም አዲሱን መርሃግብር የመቀበል ግዴታ እንዳለባት ገልፀዋል፡፡
ካልካባ ቻምፒዮናው ከተራዘመው ኦሊምፒክ በፊት መካሄዱ ለአትሌቶች ጥቅም እንደሚኖረው የገለፁ ሲሆን ውድድሩ በተከለሰው የኦሊምፒክ ማጣሪያ መርሃግብር ውስጥ እንደሚካተት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ውድድሩ የኦሊምፒክ ማጣሪያ(ሚኒማ) ለሚፈልጉ አትሌቶች ጠቃሚ ይሆናል›› ያሉት ካልካባ የዓለም አትሌቲክስ የኦሊምፒክ ማጣሪያ መርሃግብር እስከ ቀጣዩ ዓመት ሰኔ ወር እንዲራዘም ግፊት ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ስጋት የተነሳ የአትሌቲክስ ስፖርት የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድሮች እስከ መጪው ታህሳስ ወር ድረስ እንዳይካሄዱ የዓለም አትሌቲክስ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ እስከ ተጠቀሰው ጊዜ የሚካሄዱ ማንኛቸውም ውድድሮችና ውጤቶች የኦሊምፒክ ማጣሪያም ይሁን እውቅና እንደማያገኙ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡ ይህ የዓለም አትሌቲክስ ውሳኔ በበርካታ ታላላቅ የዓለማችን አትሌቶች የሰላ ትችት ሲሰነዘርበት እንደሰነበተ ይታወቃል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የስፖርቱ ዓለም ካለፉት ሁለት ወራት በላይ እንቅስቃሴው ተገድቦ ቢቆይም ከቅርብ ቀናት ወዲህ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው ለመመለስ ሲፍጨረጨሩ እየተስተዋለ ነው፡፡ ታላላቆቹን አውሮፓ እግር ኳስ ሊጎች ጨምሮ አንዳንድ አገራትም ስፖርታዊ ውድድሮቻቸውን ለማስጀመር ከቫይረሱ ስጋት ነፃ ሳይሆኑ ጥረት እያደረጉ ሲሆን አብዛኞቹ ውድድሮችን በዝግ ስቴድየሞች በማድረግ የውድድር ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት መርሃግብሮቻቸውን ስለመፈፀም እየተጨነቁ ይገኛሉ፡፡
በርካቶቹ የዓለም አቀፍ ውድድሮች ግን ቀደም ሲል ቫይረሱ በቀጣዩ ዓመት ይጠፋል ወይም በቁጥጥር ስር ይውላል በሚል ተስፋ ወደ ቀጣይ ዓመት እንዲዞሩ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡ ከነዚህ መካከል በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ዘግይቶም ቢሆን በቫይረሱ ስርጭት ስጋት የተነሳ ታላቁን የስፖርት መድረክ ለአስራ ስድስት ወራት እንዲራዘም ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህም እንደሌሎቹ ውድድሮች ሁሉ ቫይረሱ በቀጣዩ ዓመት በቁጥጥር ስር ይውላል ከሚል ተስፋ እንጂ በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ አልነበረም፡፡ በርካቶቹ ይህን ተስፋ የሙጥኝ ብለው እያንዳንዱ ቀን እንደ ዓመት እየረዘመባቸውም ቢሆን ቀጣዩን ዓመት በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ግን በተቃራኒው እየቀነሰ ከመሄድ ይልቅ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህንን ያስተዋሉ የጤና ባለሙያዎችም ለአስራ ስድስት ወራት የተራዘመው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በቀጣዩ ዓመት ላይካሄድ እንደሚችል ከወዲሁ እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ የኦሊምፒኩ አዘጋጅ የሆነችው ጃፓን የተላላፊ በሽታዎች ፕሮፌሰር የሆኑት ኬንታሮ ዋታ የቫይረሱ ስርጭት ኦሊምፒኩ በተራዘመበት ወቅት በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ አጠራጣሪ በመሆኑ ውድድሩ ላይካሄድ እንደሚችል ስጋታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
በዓለም ላይ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከተስፋ በስተቀር የቫይረሱ ስርጭት በጊዜ የሚገታ ወይም ፈውስና ክትባት በዚህ ጊዜ እውን ይሆናል የሚያስብል እንዳልሆነ መታዘብ ይቻላል፡፡ ይህንን ከግምት ያስገቡት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቶሺሮ ሙቶ ኦሊምፒኩ የቫይረሱን ስጋት ለማምለጥ በአስራ ስድስት ወራት ቢራዘምም ከቫይረሱ ተፅዕኖ ሊያመልጥ እንደማይችል ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማመልከታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮናም ከዚህ የተለየ እድል እንደማይገጥመው ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡