የቀድሞ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቅሬታ ቀረበባቸው

የቀድሞ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቅሬታ ቀረበባቸው

የምናገርበትን ‹‹ድምፀት›› ካለመረዳት የቀረበ ቅሬታ ነው ብለዋል

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞ የዋሊያዎቹ አለቃ ሰውነት ቢሻው፣ ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው መክፈል ስለሚገባቸው ወርኃዊ ክፍያ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት ቅሬታ ቀረበባቸው፡፡ አቶ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው፣ የቀረበው ቅሬታ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የተናገርኩበትን ‹‹ድምፀት›› (ቶን) ካለመረዳት የቀረበ ነው ሲሉ ቅሬታውን እንደማይቀበሉት ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን ግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባስገባው የክስ ደብዳቤ፣ አቶ ሰውነት ቢሻው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ሳለ፣ መንግሥት በጊዜያዊ አዋጅ ያወጣው ማንኛውም መሥሪያ ቤትም ሆነ ድርጅት ሠራተኞችን ማሰናበት እንደማይችል፣ ደመወዝ መክፈል የግድ እንደሆነና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ የሊግ ኮሚቴው የተጨዋቾች ደመወዝ መከፈል እንዳለበት እያሳሰቡ እያለ፣ የመንግሥትንም ሆነ የፌዴሬሽኑን እንዲሁም የሊግ ኮሚቴውን ውሳኔ የሚቃረን ተግባር ፈጽመዋል ብሏል፡፡

‹‹እግር ኳስ ተጨዋቾችን ከአገሪቱ ሕዝብ ነጥለን አናያቸውም፡፡ መንግሥት ገንዘብ ከሌለው የለውም፣ ኳስ ተጨዋች ከማንም በላይ አይደለም፣ መንግሥትን አምነህ፣ ክለቦችን አምነህ፣ እንደፈለግክ የምትዝረከረክበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡ ሕዝብ እያለቀ ደሞዝ አይጠየቅም፤›› ብለዋል በሚል ከሷል፡፡ ማኅበሩ እንዲያውቁት ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለስፖርት ኮሚሽንና ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በግልባጭ አሳውቋል፡፡

አቶ ሰውነት በበኩላቸው፣ ‹‹ማኅበሩ ወደ እንደዚህ ዓይነቱ ውሳኔ ከመሄዱ በፊት ከተጨዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር በተገናኘ አቶ ሰውነት በምን ጉዳይ ምን እንደተናገሩ፣ የተናገሩበት ድምፀት እንዴትና ምን ይመስል ነበር፣ በእያንዳንዱ አስተያየት የነገሮች መነሻና መደምደሚያ ምን እንደሚል ማዳመጥና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነገሩን በግርድፉ መረዳትና መናገር ከሕግም ሆነ ከሞራል አኳያ ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ በየትኛውም መመዘኛ ተጨዋች ደመወዝ አይከፈለው የሚል መንፈስ ያለበት ንግግር አልተናገርኩም፣ ልናገርም አልችልም፡፡ ምክንያቱም ዕድሜ ልኬን ተጨዋቾች እንዲጠቀሙና እንዲያድጉ ስሠራ የኖርኩ ሰው ነኝ፤›› በማለት ቅሬታው የእሳቸውን ሰብዕና የማይገልጽ በመሆኑ ክሱን እንደማይቀበሉት ያስረዳሉ፡፡

አቶ ሰውነት ‹‹ተናገሩት›› የተባለው አስተያየት ሙሉ ቪዲዮውን መመልከቱን የሚያስረዳው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለር አሶሴሽን በበኩሉ፣ ‹‹የተጨዋቾችን ወርኃዊ ክፍያ በውላቸው መሠረት መከፈል እንደሚገባው ከተጨዋቾቹ በላይ ግንባር ቀደም ተከራካሪ መሆን ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ክፍያ እንዳይከፈላቸው ያሏቸው ተጨዋቾች ከእሳቸው ጋር ብዙ ነገር የሠሩ ለመሆናቸው ከእሳቸው በላይ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ቪዲዮው ስላለ መመልከትና ማረጋገጥ ይቻላል፤›› በማለት አቶ ሰውነት የሚያቀርቡትን መከራከሪያ አይቀበልም፡፡

‹‹እርግጥ ነው የአገሪቱ ክለቦች 99 በመቶ የመንግሥት በመሆናቸው፣ ክለቦች ገንዘብ ከሌላቸው ከየት ይመጣል ብያለሁ፣ ይህ ደግሞ አሁን ላይ ችግሩ እያስከተለ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመነሳት ሁሉም ሰው የሚጋራው ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም ደመወዝ ባይኖርና ገቢ ብናጣ የመንግሥትን እጅ መጠበቅ ካልሆነ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም፣ ገንዘብ ከሌለ ምንድነው የሚኮነው አልኩ እንጂ ተጨዋቾች አይከፈላቸው አላልኩም፤›› የሚሉት የፌዴሬሽኑ አመራርና የቀድሞ የዋሊያዎቹ አለቃ አቶ ሰውነት፣ ‹‹ችግሩ እንደ አገር ሁሉንም የሚመለከት በመሆኑና ተጨዋቾችም የኅብረተሰቡ አካል በመሆናቸው ምናልባት የተናገርኩበት ‹‹ድምፀት›› እንጂ ክፍያ እንዳይከፈላቸው የሚል እምነቱም ፍላጎቱም ሊኖረኝ አይችልም፤›› በማለት ቅሬታውን ያጣጥሉታል፡፡ ስም የማጥፋት ዘመቻው የሚቀጥል ከሆነ መረጃዎችን አደራጅተው መብታቸውን በሕግ የሚያስከብሩ ስለመሆኑ ጭምር ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ከተጨዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር ተያይዞ ከክለቡ ተጨዋቾች ጋር ተወያይቶ ስምምነት ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡ እንደ ክለቡ ምንጮች ከሆነ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያስከተለ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አኳያ፣ ክለቡም ሆነ ተጨዋቾቹ ሳይጎዱ ችግሩን በጋራ ለመከላከልና ለማለፍ፣ ተጨዋቾቹ ቀደም ሲል ካልተከፈላቸው የሁለት ወር ደመወዝ ውስጥ የአንድ ወር ክፍያ ብቻ እንዲከፈላቸው ተስማምተዋል፡፡  

እስከ ሰኔ ወር ያለውን ክፍያ በሚመለከት ደግሞ ሁሉም ተጨዋቾች ይከፈላቸው ከነበረው ወርኃዊ ክፍያ 40 በመቶው ተቀንሶ ለክለቡ ገቢ ለማድረግ መስማማታቸውም  ጭምር ተነግሯል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ከስፖንሰርና ከደጋፊዎች በሚያገኘው ገቢ የሚተዳደረው አንጋፋው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ፣ በችግሩ ምክንያት የተጨዋቾችንም ሆነ ሌሎች ሠራተኞችን ወርኃዊ ክፍያ ሳያስተጓጉል እንደሚከፍል ባለፈው ሳምንት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡