«ተምዘግዛጊው ሚሳኤል» ተስፋዬ ኡርጌቾ አረፈ!

«ተምዘግዛጊው ሚሳኤል» ተስፋዬ ኡርጌቾ አረፈ!

ከአዲስ አበባ በ110 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ወንጂ ከተማ በእግር ኳሱ በርካታ ተጫዋቾችን ማፍራቷ ይነገርላታል።

ከአዲስ አበባ በ110 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ወንጂ ከተማ በእግር ኳሱ በርካታ ተጫዋቾችን ማፍራቷ ይነገርላታል። ይህም ከተማዋ ከምትታወቅበት ጣፋጭ የሸንኮራ አገዳ አምራችነቷ፣ የስኳር ፋብሪካ ማዕከልነቷ ትይዩ የእግር ኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያ አሰኝቷታል። የወንጂን ከተማ በእግር ኳሱ ካስተዋወቁት ተጫዋቾች መካከል ደግሞ አንጋፋው ተጫዋች ተስፋዬ ኡርጌቾ ይጠቀሳል። በወንጂ ከተማ ተወልዶ ያደረገው ተስፋዬ፤ በእግር ኳሱ ትልቅ ቦታ መድረስን የልጅነት ህልሙ አድርጎ የተነሳ መሆኑን የቅርብ ወዳጆቹ ይናገሩለታል። ከልጅነቱ ጀምሮ ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር በመያዝ መነሻው ከሰፈር ሜዳ ነበር። በኳሱ የመጓዝ ህልሙ ሩቅ የሆነው የትናንቱ ታዳጊ ተስፋዬ፤ በስፖርቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማጎልበቱ ወደ ክለብ እንዲያድግ አጋጣሚን አገኘ።
ከከተማዋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሠረት አንዱ የሆነው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ያቋቋመውን «የወንጂ ስኳር እግር ኳስ ክለብ» ነበር የተቀላቀለው። ተስፋዬ የወንጂ ስኳርን መቀላቀሉ በኳሱ ለሚያልመው ህልሙ፣ ለሰነቀው ተስፋ እውን መሆን መንደርደሪያውን የትውልድ ከተማው ሆነለት። ከክለቡ ጋር የተወሰኑ ጊዜያትን ቆይታ ካደረገ በኋላ የሕይወቱ አቅጣጫ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋገረ። በወንጂ ስኳር እግር ኳስ ክለብ በፈጣንና ጥበብ የተሞላበት እንቅስቃሴ ባለቤትነቱ በአየር ኃይል እግር ኳስ ቡድን እይታ ውስጥ አስገባው። በወቅቱ የአየር ኃይል አሰልጣኝ የነበረው አንጋፋው አሰልጣኝ ሀጎስ ደስታ ልብ በማሸነፍ አሰልጣኙ አየር ኃይልን እንዲቀላቀል አስቻለው። በእግር ኳሱ ትልቅ ደረጃ የመድረስ ተስፋ በልቡ ሰንቆ ወደሜዳ ለሚመጣው ታዳጊ ትልቅ ዕድል ነበር።
በአየር ኃይል ቤት ተስፋዬ ምኞቱን መኖር ለመጀመሩ መንደርደሪያው ነበር። በቡድኑ ውስጥ ያሳየው እንቅስቃሴ ክለቡ እንዲደሰትበት ከማድረግ አልፎ፤ ለብሔራዊ ቡድን እንዲጫወት ሀገራዊ ጥሪ እንዲቀርብለት አድርጎታል። በ1983 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ በግብጽ አዘጋጅነት በተካሄደው 7ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ችሏል። የወንጂው ፍሬው ተስፋዬ የስኬት ጀንበርን በአጭር ጊዜ ውስጥ መመልከት የቻለ ሲሆን፤ በሜዳ ላይ የሚያሳየው ብቃትና የተላበሰው መልካም ስብዕናው ተደምረው ጉዞው ያማረ እንዲሆን አደረጉት። የወጣት ብሔራዊ ቡድኑ በሻምፒዮናው ላይ ከተሳትፎ መልስ የተስፋዬ የክለብ መዳረሻ ከአየር ኃይል ተወርውሮ ወደ አንጋፋው ቅዱስጊዮርጊስ ላይ አረፈ። በ1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አንፀባራቂ ታሪክ ባላቸው በኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ አማካኝነት ክለቡን ተቀላቀለ። የእግር ኳሱ ጥበበኛ ተስፋዬ ፈረሰኞቹን መቀላቀሉ በኳሱ የስኬትን ቁንጮ ለመቆናጠጥ ትልቅ ዕድል ፈጥሮለታል። በአማካይና የተመላላሽ ቦታዎች ላይ በመጫወት ክለቡን ለስኬት ማብቃት በመቻሉ የክለቡ ደጋፊዎች ዛሬም ድረስ ትልቅ ቦታ እንዲኖራቸው አድርጓል።
ከ1983 ዓ.ም እስከ 1992 ዓ.ም ፈረሰኞቹን ማገልገል የቻለው አመለሸጋው ተስፋዬ፤ በቆይታው ከፍተኛ ዝናና ተወዳጅነት አትርፏል። በፈረሰኞቹ ቤት በቆየባቸው የሰባት ዓመታት ቆይታ ውስጥ በ1986 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሻምፒዮን ኮከብ ተጫዋችነትን ክብር አግኝቷል። ክለቡ ቅዱስጊዮርጊስ ከ1986 እስከ 88 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሻምፒዮናነትን ክብር ሲቀዳጅ ግብ አስቆጣሪ ከሆኑት ተጫዋቾች ጀርባ የእርሱ ሚና ግዙፍ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ተጫዋቾች መስክረውለታል። ከክለቡ ስኬት ተሻግሮም ለሚወዳት ሀገሩ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተመርጦ በርካታ ጨዋታዎችን ተጫውቶ አሳልፏል።
በ1985 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ናይጄሪያን 1ለ 0 ስታሸንፍ ብቸኛዋን ግብ በማስቆጠር ሀገሩን ለድል ያበቃበት አጋጣሚ በአብዛኛው የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ ይታወሳል። በብሔራዊ ቡድን ብሎም በክለብ ደረጃ የነበረው እንቅስቃሴ ከክለቡ ተሻግሮ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ከፍተኛ ተደናቂነት ማትረፍ የቻለ ተጫዋች ነበር። በሀገር ውስጥ የክለብ ፍልሚያዎች በፈረሰኞቹ ቤት በ4 ቁጥር ማሊያ መንገስ ችሏል። በሜዳ ላይ ፈጣንና ድንቅ እንቅስቃሴ የሚያሳይ መሆኑን ተከትሎ «ተምዘግዛጊው ሚሳኤል» የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ተስፋዬ፤ ከሀገር አልፎ ወደ አውሮፓም አምርቶ በፊንላንድ ሊግ መጫወት ችሏል። በኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ዛሬም ድረስ እንደ ብርቅ በሚታየው የአውሮፓ ሊግ የኳስ ጥበበኛው ተስፋዬ ባህር ተሻግሮ።
እግር ኳስን በተጫወተባቸው ዓመታቶች በመሀል ሜዳ የጨዋታ ብቃቱ የብዙዎቹን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ቀልብ ይስብ የነበረው፤ ተስፋዬ የተጫዋችነት ዘመኑን ቢያበቃም ከኳሱ አልተለየም ነበር። ከተጫዋችነት ወደ አሰልጣኝነት የሕይወቱ አቅጣጫ ተሸጋገረ። በአሰልጣኝነትም ሕይወት በመሰማራት የጌታ ዘሩን የታዳጊ ፕሮጀክት እና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲንም ክለብን በመያዝ አሰልጥኗል። የሕይወቱን ፍጻሜ ከኳስና ከእናት ሀገሩ ለመነጠል ፍላጎት ያልነበረው ተስፋዬ፤ መኖር ግድ ነበርና በአሜሪካ በስደት በርካታ ዓመታትን አሳልፏል። «ተምዘግዛጊው ሚሳኤል» በገጠመው ህመም ከሚኖርበት አሜሪካ የመጣ ሲሆን፤ በሚወዳት ሀገሩ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ግንቦት 05 ቀን 2012 ዓ.ም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕይወቱ አርፏል። በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ማሳረፍ የቻለው ተስፋዬ የቀብር ሥርዓቱ በትውልድ ከተማው ወንጂ ሸዋ ኪዳነ ምህረት ከትናንት በስቲያ ተፈጽሟል። የተስፋዬ ሞት ብዙዎቹን ያሳዘነም ሲሆን የዝግጅት ክፍላችን በተስፋዬ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹ ለወንድሙ ተከተል ኦርጌቾና ለመላው ስፖርት አፍቃሪ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች መፅናናትን ይመኛል።