የኢትዮጵያ ቨርቸዋል ሩጫ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ቨርቸዋል ሩጫ ተካሄደ

ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያሳደረውን ተፅዕኖ መቀነስና መቀየር ይቻል ዘንድ በኢንተርኔት የታገዘ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የቨርቿል ሩጫ ተካሄደ።

ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያሳደረውን ተፅዕኖ መቀነስና መቀየር ይቻል ዘንድ በኢንተርኔት የታገዘ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የቨርቿል ሩጫ ተካሄደ። በኢንተርኔት የታገዘ የቀጥታ ቪዲዮ «ቨርቿል ሩጫ» መርሐ ግብር በተሳካ ሁኔታ ከትናንት በስቲያ መካሄዱን የሩጫ አዘጋጁ የታላቁ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ አስታውቋል። በቨርቹዋል ሩጫ መርሐ ግብሩ ላይ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ስለሺ ስህን፣ ፋጡማ ሮባ፣ ሚሊዮን ወልዴ እና እጅጋየሁ ዲባባ መሳተፋቸው ታውቋል። በውድድሩ አንድ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ከመላው ዓለም ሆነው ዙም በተሰኘ መተግበሪያ ላይ በኢንተርኔት በቀጥታ እየተያዩ በቤታቸው እና ግቢያቸው ውስጥ ሆነው በመሮጥ እና ሶምሶማ በማድረግ ተሳትፈውበታል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ቨርቹዋል ሩጫ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ፤ የኮቪድ-19 በሽታ በዓለም ዙሪያ ከፈጠረዉ የጤና ፈተና ጎን ለጎን፣ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጫና አስከትሏል። በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ረዘም ላለ ጊዜ ቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገደዋል። በመሆኑም የወገኖቻችንን ችግር በተወሰነ መልኩ ማቃለል ይቻል ዘንድ በኢንተርኔት የታገዘ ቨርቿል ሩጫ ማዘጋጀት አስፈልጓል ብለዋል፡፡
በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ በበረታባቸው አሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮያዊያን ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤ በወጣ ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ቤት ውስጥ ለመቀመጥ በመገደዳቸው ሥራን እንደ ወትሮው ወጥቶና ነፃ ሆኖ መሥራት አልተቻለም። ስለዚህ በበርካቶች ላይ ስጋትና የአዕምሮ ጭንቀት በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ጋሻው፤ ጫናውን በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ የሚያግዝ በኢንተርኔት በቤትና ግቢ ውስጥ ሆነው የሚሮጡት የቨርቹዋል ሩጫ ተዘጋጅቶ በስኬት መከናወኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ቨርቹዋል ሩጫ ላይ አንጋፋና ብርቅዬ አትሌቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መሳተፍ የቻሉ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ጋሻው ፤ከዝግጅቱ የተገኘው ገቢ በኮቪድ-19 ዙሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሠሩ ሁለት መንግሥታዊ ያልሆኑና በኢትዮጵያዊያን ለሚመሩ አነስተኛ ድርጅቶች የሚበረከት መሆኑንም ተናግረዋል።
በሩጫው ላይ አትሌቶች በያሉበት ቦታ ሆነው በቪዲዮ ተራ በተራ እየሮጡ ለውድድሩ በተዘጋጀ መተግበሪያ ላይ በቀጥታ በማህበራዊ ሚዲያ ከተሳታፊዎች ጋር ሩጫውን አካሄደዋል። ተሳታፊዎችም በቤትና ግቢ ውስጥ እንዲሁም የመሮጫ ማሽን ላይ በመሆን እየሮጡ በስልካቸው፣ በኮምፒዩተርና በሌሎች የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በመታገዝ አትሌቶችን እየተከተሉ ሮጠዋል። በፌስቡክ እና ዩቲዩብ ላይቭ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ ላይ ሆነው በኢንተኔት በታገዘው ሩጫ ላይ ካሉበት ሆነው መሳተፋቸው ታውቋል።
ቨርቹዋል ሩጫ (Virtual Race) የሚባለው ከየትኛውም ቦታ እና አካባቢ በመሆን የሚከናወን ሩጫ ወይንም ፈጠን ያለ የዕርምጃ ውድድር እንደማለት ነው።