“ህወሓትንና የትግራይ ህዝብን በአንድ ላይ ማየት የተሳሳተ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ”- አቶ ደረጀ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር

“ህወሓትንና የትግራይ ህዝብን በአንድ ላይ ማየት የተሳሳተ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ”- አቶ ደረጀ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር

ህወሓትንና የትግራይ ህዝብን በአንድ ላይ ማየት የተሳሳተ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር አስታወቁ። ህወሓት/ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ የበላይነቱን ለማንጸባረቅ ብቻ የሚንቀሳቀስ ቡድን መሆኑን አመለከቱ።

ሊቀመንበሩ አቶ ደረጀ በቀለ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት ፣ህወሓት አንድ ነን እንደሚለው፤ ህወሓትንና የትግራይ ህዝብን በአንድ ላይ ማየት የተሳሳተ ነው።

ቀደም ባለው ጊዜ እኔም ከህወሓት አመራሮች ትርክት ተነስቼ የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው ብዬ አስብ ነበር ያሉት ኃላፉው ፣አሁን ውስጡ ገብቼ እንዳየሁት ግን በጣም የተራራቁ ናቸው። የህዝቡ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ሲሆን ጥቂት የህወሓት አመራሮችና እነርሱን ተጠግተው ያሉ ግን በጣሙን ከህዝቡ የራቀና ሊነጻጸርም በማይችል የናጠጠ ኑሮ ውስጥ እንደሚኖሩ አመልክተዋል።

እኔም ትግሬ ሁሉ የተጠቀመ፤ ትግሬ ሁሉ የህወሓት አባል የሆነ አድርጌ ሳይ የነበረበት ሁኔት የተሳሳተ መሆኑን አይቼ ታርሜአለህ የሚሉት አቶ ደረጀ፣ ይሄን ምስል ያስያዘኝ የህወሓት አሳሳች የሴራ ምስል መሆኑን በተግባር አረጋግጫለሁ ብለዋል።

“ህወሓት በከተማ ውስጥ እንጂ በገጠር የለም። ይሄንንም ከመቐሌ እስከ ደደቢት እና ዛላንበሳን ጨምሮ ሌሎችም የትግራይ ክልል ክፍሎችን ባስጎበኙኝ ወቅት ተመልክቼ ተገንዝቤያለሁ። በእነዚህ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች በነበረኝ ጉብኝት የተመለከትኩት እና አንዳንዴም አማርኛ የሚናገሩ/የሚችሉ ሰዎችን አነጋግሬ እንደተረዳሁት፤ ህወሓት ከህዝቡ ጋር የለም። ምናልባት የተወሰነ ህዝብ ነው ከህወሓት ጋር ያለው” ብለዋል።

“ይሄ የተወሰነ ህዝብ ደግሞ በመቐሌ ከተማ እና ዙሪያዋ ያሉ ጥቂት ሰዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ ሌላው ቀርቶ ወደ አድዋና አክሱም ስንሄድ እውነት ለመናገር ህዝቡ የሚያሳዝን ህዝብ ነው። ምክንያቱም ሰፊው የትግራይ ህዝብ አንደኛ፣ በአሁን ጊዜ በዚህ ዘመን ለእግሩ እንኳን ጫማ የሌለው ህዝብ ነው። ልብስ በረከሰበት በዚህ ወቅት ልብስ እንኳን መልበስ ያልቻለ ህዝብ ነው። ይህ ደግሞ ጥቂት የህወሓት አመራሮችና አባላት ገንዝቡንም ለራሳቸው፤ አገሩንም የራሳቸው አድርገው እንደያዙት የሚያሳይ እንደሆነም አመልክተዋል

“በተጨባጭ እንዳየሁት የትግራይ ህዝብ መፈናፈኛ ስላጣ ዝም ብሏል። ለዚህ ደግሞ ወደ ዛላንበሳ በሄድኩበት ወቅት ያነጋገርኳቸው አንድ አዛውንት ያጫወቱኝ ትልቅ አብነት ነው። እኚህ አዛውንት እንዳጫወቱኝ፣ እዚሁ ተወልጄ የኖርኩ ነኝ፤ ነገር ግን ስርዓቱ ወይም የህወሓት አስተዳደር ለእኔም ሆነ ለአካባቢው ምንም ያደረገው ነገር ስለሌለ አብዛኛው በችግር ውስጥ ያለ፤ በዕድሜ መግፋት ምክንያት ከቤት የማትወጣው ባለቤቴም ሆነች እኔም በቤተ ክርስቲያን ዕርዳታ ኑሮዬን እየገፋሁ የምንኖር ህዝቦች ነን ነበር ያሉኝ። በህወሓት አገዛዝ ምክንያትም በርካታ ወጣቶች ከአገር ለመውጣትና ለመሰደድ ስለመብቃታቸውም ነው ያጫወቱኝ። ”

“ይሄን ከመስማቴና ክልሉን በተለይ ገጠራማውን አካባቢ ከመመልከቴ በፊት፤ እኔም የነበረኝ ግንዛቤ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች በተለየ መልኩ እንደተጠቀመ፤ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ብዙ ነገር እንዳገኘ ነበር። እንደኔ ሁሉ ሌሎችም እንዲሁ ሊያስቡ ችላሉ። እውነቱ ግን ይሄ አይደለም፤ የትግራይ ህዝብ ጭቆና ውስጥ ነው ያለው። የትግራይ ህዝብ በኢኮኖሚው አሁንም ወደኋላ የቀረ ነው። የኢኮኖሚው ችግር ደግሞ ከምግብ እስከ አልባሳት በሚፈልገው ልክ እንዳያገኝ ያገደው ህዝብ ነው። መቐሌን ጨምሮም በየከተማው ያለ ወጣትም መሥራት በሚችልበት ዕድሜውና ሰዓቱ ያለሥራ ከጠዋት እስከ ማታ በየበረንዳውና በየመንገዱ ላይ ባሉ የጀበና ቡናዎች ወንበር ላይ ተቀምጦ ዳማ እና ካርታ ሲጫወት የሚውልበትን እውነት ተመልክቻለሁ። ከዚህ በተቃራኒው ግን ጥቂት የህወሓት አባላትና ወደ ህወሓት የሚጠጉ ሰዎች የናጠጠ ኑሮ ይኖራሉ” ብለዋል።

ህውሓት የፌዴራሊስት ሄል ነኝ እያለ ከማጭበርበር ባለፈ እውነተኛ የፌዴራል ኃይል አይደለም ያሉት ሊቀመነንበሩ፣ ፌዴራሊዝም ስንልም የጋራ አስተዳደር ማለታችንም ነው። ህወሓት ግን የእኩል አስተዳደር ብሎ ነገር የለውም። ህወሓት የበላይነቱን ለማንጸባረቅ ብቻ የሚንቀሳቀስ ቡድን እንደሆነም አስታውቀዋል።

የህወሓት አመራሮች ቦረና ያለውን ከብት አርቢ ነው፤ ሶማሌ ያለውን እንዲህ ነው እያሉ ከመናገር ውጪ፤ ቦረና ያለውም ራሱን ለማስተዳደር ይችላል፤ ሶማሌ ያለውም ራሱን ለማስተዳደር ይችላል፤ እንዲሁም የአካባቢውን ልማት መምራት ይችላል ብሎ የሚያስብ ቡድን አይደለም። የራሱን የበላይነት ብቻ ለማንጸባረቅ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው። ይሄን የበላይነቱን ለማረጋገጥም በየቦታው የራሱን የስለላ መረብ በመዘርጋት የሚሠራ ቡድን ጭምር ነው ብለዋል።

ፌዴራሊዝም ማለትኮ የመጀመሪያው ጉዳይ ራስን ማስተዳደር ነው። በራስ መዳኘት ነው። በራስ ቋንቋ መማር ነው በማለት የሚናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ህወሓት ግን ያንን ለይምሰል ይናገር እንጂ ውስጥ ገብተን ስናየው የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚጨፈልቅ ቡንድ ነው። ይሄንን መብት ጨፍልቆም እሱ እንዴት መግዛት እንደሚችል የሚያስችለውን የወጥመድ መረብ የሚዘረጋ ነው።

የዚህ ጨፍላቂነቱ ማረጋገጫ የሚሆነው ደግሞ፤ እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎች ምርጫ አናካሂድም በሚሉበት ወቅት እርሱ አካሂዳለሁ ማለቱ የራሱን የበላይነት ለማንጸባረቅ የሚያደርገው ድርጊት ነው። ከዚህ ባለፈ ስለ ህዳሴው ግድብ ያገባናል ብለን ሁላችንም ፓርቲዎች ስንናገር፤ ስለሱ ጉዳይ መንግሥትን እንጂ እኛን አይመለከትም ማለቱ ነው። ይሄን የሚል ድርጅት ደግሞ የፌዴራሊዝም ጠበቃ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ይህ ፕሮጀክት ከዳር እስከዳር ያሉ የፌዴራል መንግሥቱ አባል ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ያሉ ህዝቦች ፕሮጀክት ሆኖ ሳለ፤ ይሄን የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሀብት ስለሆነው ግድብ አያገባንም ብሎ መናገር አግባብነት የሌለው፣ ስለፌዴራሊዝም የማያስብና የራሱን ኑሮ ብቻ ለማንቀሳቀስ የሚጥር ድርጅት መሆኑን ነው የተረዳሁት ብለዋል።