የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በመቀሌ ግድያ የተፈጸመበት ወጣት የዴሞክራሲ ዕጦት ማሳያ ነው አለ

የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በመቀሌ ግድያ የተፈጸመበት ወጣት የዴሞክራሲ ዕጦት ማሳያ ነው አለ

በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ በጠራራ ፀሐይ ክልሉን እየገዛ ባለው ፓርቲ ሕወሓት የታጠቁ ኃይሎች በጥይት ተደብድቦ በተገደለው ወጣት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ድርጊቱን በማውገዝ፣ የወጣቱ ሞት የሚያሳየው በክልሉ ውስጥ የሰላምና የዴሞክራሲ ዕጦት ማሳያ ነው ሲል የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ በጠራራ ፀሐይ ክልሉን እየገዛ ባለው ፓርቲ ሕወሓት የታጠቁ ኃይሎች በጥይት ተደብድቦ በተገደለው ወጣት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ድርጊቱን በማውገዝ፣ የወጣቱ ሞት የሚያሳየው በክልሉ ውስጥ የሰላምና የዴሞክራሲ ዕጦት ማሳያ ነው ሲል የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡

እሑድ ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. የመቀሌ ከተማ ፖሊስ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ቁጥጥር ሲያደርግ በተፈጠረ አለመግባባት አንድ ወጣት ሲገድል፣ ሁለት ወጣቶች ቆስለው በሕክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ቀደምም የመቀሌ ከተማ ፖሊስ አንድ ሰው መግደሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ድርጊቱ በመደገሙ ሳቢያ የከተማው ነዋሪዎች ተቃውሞ ማሰማታቸው ታውቋል፡፡

የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ሰላም ወዳዱና እንግዳ አክባሪ የሆነው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ መሪር የሐዘንና የውጥረት ድባብ ውስጥ እንደሚገኝ፣ ይህ ክቡር የሰው ሕይወት የጠፋበትና ከባድ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመበት ክስተትም ሰላምንና ፀጥታን በሕግ አግባብ ለማስጠበቅ ኃላፊነት በተሰጠው የፀጥታ አካል የተፈጸመ መሆኑ እጅግ በጣም አሳዛኝ ያደርገዋል ብሏል።

‹‹ይህ ድርጊት ብዙ መስዋዕትነት ለከፈለው የትግራይ ሕዝብ የማይገባው ነው፡፡ በመሆኑም የወጣቱ ግብረ መልስም በክልሉ ሰላምና ዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ የእኔ ጉዳይ ነው የሚል ከፍተኛ የሰላም፣ የልማትና የለውጥ ፍላጎቶችና ቁርጠኝነት እንዲሁም ዝግጁነት መኖሩን በግልጽ አሳይቷል፤›› ያለው ፓርቲው፣ ከቀናት በፊት የተከሰተው የአንድ ወጣት ሕይወት ሕልፈትና የሁለት ወጣቶች የመቁሰል አደጋ፣ በክልሉ ውስጥ የሰላምና የዴሞክራሲ ዕጦት ማሳያ መሆኑን አስታውቋል፡፡

‹‹እንደሚታወቀው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማስተዳደርና የማስፈጸም አግባቦች ውስጥ የሰው ልጅን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና በሕግ የማስከበር ተግባር ላይም የፀጥታ አካላት የላቀ ሰብዓዊነት፣ ታጋሽነትና፣ ፍፁም ሕዝባዊነት የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል። የዴሞክራሲና የተሻለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልምድ ጉዳይ ከአስተምህሮት ሥርፀትና ግልጽ ተጠያቂነትን ከማስፈን አሠራር ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ጉዳይ ሲሆን፣ ዜጎች በመንግሥታቸው የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ቢሆንም፣ እንዳለመታደል ሆኖ በትግራይ ክልል በወቅቱ ከሚስተዋሉ ሕገወጥ ክስተቶች አፈናና ግልጽ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዳለ ማስተዋል ተችሏል፤›› ሲል አክሏል፡፡

በተለይ ራሳቸውን ለመከላከል በማይችሉ ወጣቶች ላይ መተኪያ የሌለውን ክቡር ሕይወታቸውን እስከ መቅጠፍ የደረሰ የኃይል ዕርምጃ በየትኛውም መለኪያ መወገዝ ያለበትና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እኩይ ተግባር መሆኑን፣ ድርጊቱም በፍጥነት ተጣርቶ የተወሰደው የዕርምት ዕርምጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አጥብቆ እንደሚጠይቅ ፓርቲው አስታውቋል፡፡