ከሳይንስ የራቁ ሳይንቲስቶች

ከሳይንስ የራቁ ሳይንቲስቶች

ከሳይንስ የራቁ ሳይንቲስቶች

  • ‘ምንም አይነት የጋራ እሴት የለንም’ ብሎን በማግስቱ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ምርጫ ቦርድን የሚወጥር፣
  • ‘ሁለት መንግስት ነው ያለው፤ አንዱ እኔ ነኝ!’ የሚል ኢንተርቪው የሚሰጥ፤ እሱ መስጠት የማይፈልገውን ክብር ከሌሎች የሚፈልግ፤
  • ዐቢይ አህመድ ዱባይ ጎዳናዎች ላይ ሲታይ ጂኦፖለቲካሊ ሊተነትን የሚያምረው የራሱን ሳውዲ መመላለስ ኢንተርፐርሰናሊ የሚያይ፣
  • እሱ በደጋፊዎቹ የሚሞላውን አዳራሽ፤ ተቃዋሚዎቹም እንደሚያደርጉት የሚዘነጋ፣
  • ታጣቂ ቡድን ሲታገል ድጋፍህን እየሰጠህ፤ መንግስት ታጥቆ ሲመክት የሚኮንን፣
  • ለማ መገርሳን “ለኦሮሞ ህዝብ ባለውለታ፤ ለጸረ ህወሓት ትግሉ የማይተካ ሚና የነበረው” ብሎ በማሞከሸትና “ዐቢይ አህመድ የህወሓት አሽከር ነበር” ብሎ በማኮሻሸት መሀል ያለ፤

ሳይንቲስቱ ጃዋር መሀመድ ሲራጅ፤ ግራ ገብቶታል። ግጥሚያውን የቻለው አይመስልም። ከራሱ ቅኝት የሚያወጣ ትግል ገጥሞት የስትራቴጂስትነት ሰርቲፊኬቱን ሲፈልግ ከርሟል። ስለሌለ አላገኘውም። ‘ታክቲካሊ ሱፐር፤ ቴክኒካሊ ጂኒየስ’ ሲሉትና ሲለን የነበረውን እብጠት የሚያስተነፍስ ቅርቃር ውስጥ ነው። ማታ ያስፈራራና፤ ጧት ‘አስፈራራችሁኝ’ ይላል። ማታ ጥዶ፤ ጠዋት ‘አገነፈሉብኝ’ ይላል።

 ፖለቲካዊ እጥፋቶቹ ከአንዲት ትንሽዬ የገጠር መንደር ተነስቶ፤ በጥቂት አመታት ውስጥ ኤዥያን በትምህርት ያካለለውን ወጣት አይመስሉም። በስታንፈርድና በኮሎምቢያ ጅረቶች የታጠበ አይመስልም። ይቸኩላል፤ ይጣዳፋል። ይስገበገባል። የጉራ መቆጣጠሪያ ቫልቩ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። 

ቃለ መጠይቁ ላይ “ስታንፈርድ እያለሁ ወደ ኦክስፎርድ ሄጄ ነበር፤ እዚያ በነበርኩበት ወቅት የነበረኝን ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ያሳለፍኩት ፓሮኪያል ፓርቲ ፖለቲክስ ሳጠና ነበር” ይላል። ስልጣነ መጠይቁ ላይ ግን፤”አለዚያ ሀገራዊ ቀውስ ይፈጠራል” ይላል። ጃል ዳውድን ሰምቶ መማር ይሄን ያህል ከባድ ነውን? የሀይሌ ፊዳን ልጆች አይቶ ታክቲካሊ ብልጥ መሆንና ድልድይ ሆኖ ማለፍ መሸነፍ ነው? እነ መረራ ትግል ሲጀምሩ ያነገቡትን የሽግግር መንግስት ጥያቄ የሚመስል መፈክር ይዞ መገኘት ነው ሳይንስ?

 ጃዋር ፖለቲካዊ ሞቱን በሚገርምና በሚያሳፍር ፍጥነት ካከናወኑ ማንነቶች አንዱ ነው።  ሞቱን በይፋ የጀመራት፤ “ኢህአዴግ ከተዋሃደ ሀገር ይፈርሳል!” ሲለን ነበር። አልፈረሰም። “ፓርቲ ሆንኩ” አለና ሞቱን አካለባት። “ፖለቲካው በቃኝ! ሚዲያውን አጠናክሬ እቀጥላለሁ!”። ትንሽ ቆየና፤ “ሚዲያው ብቻ ለመታገል አይመቸኝም፤ ወደ ፓርቲ ተቀላቅያለሁ!” አለ፤ ፖለቲካው በቃኝ፤ ሲለንም “ፖለቲካው ይሻለኛል” ሲለንም እዚያው ሚዲያው ላይ ነበር። ፖርቲውን ተቀላቅሎም እዚያው ሚዲያው ላይ ነው!

ጃዋር  ጠላቶቼ ከሚላቸው ለሚሰነዘሩበት ትችቶች ሁሉ ማረጋገጫ የሰጠ Contemporary Hoax ሆኗል። Political DEEPFAKE! ህያው Piltdown Man! ጃዋር  ማለት ለራሱ፤ በራሱ ውብ ልሳን የተተረከ ፌክ ኒውስ ማለት ነው። ልቡን በአፉ ዲስኢንፎርም ያደረገ ኮስሞፖሊታን  አጭቤ። ሰልፍ ሲያይ ሳይንሱን አራግፎ የጣለ ብልጭልጭ ፉርጎ ነው።

 “የለውጡ ጌታ ነኝና ሰልጣን ይገባኛል”

እሱ አንደሚለው የለውጡ ‘ጌታ’ አይደለም። ለውጡ የአንድ ጌታ አይደለም። የጌቶች ነው። የብዙ ጌቶች። ለውጥ የቡድን ስራ ነው። ቡድኑ ውስጥ ከፊት ይታዩ ከነበሩት መካከል አንዱ ጃዋር ነበር። የጃዋር ችግሩ ሚናውን ትንሽ ያጋንነዋል። አግዝፎም አይቶታል። ወይም እያሳነሱበት እልህ ውስጥ ሳይገባ አይቀርም። በራሱ ችግርም ሆነ በእልህ ማግዘፍ ስህተት ነው። የማግዘፍ ወይም የማጋነን ትልቁ ጉዳቱ ትክክለኛውን ምስል መጋረዱ ነው። ፓወር ፒለቲክስን ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመነጭ ችግር ነው።

በ2015 በሴራ በጠቀለለው ሚዲያ በኩል፤ የህወሓትን ሚስጥር በማጋለጥና የተቃውሞ ድምጽ በመሆን ብቻ የለውጡ አንደኛ መሪ ነኝ ብሎ ማሰብ የሂሳብ እውቀት እጥረት እንዳለ ነው የሚያሳየው። ይህቺን ሸቃባ ካልኩሌተሩን ስራ እንድታቆም ካላደረገ ቆሞ መቅረቱ ነው። 

 በእርግጥ ጃዋርን ለውጡ ውስጥ የለህበትም የሚል ካለ ሀኪም ቤት መውሰድ ነው።  ብድግ እያሉ “እኛ ነን የለውጡ ሞተሮች” የሚሉ የእሱ ብጤዎችንም ማረጋጋት ያሻል።

 ጃዋር የረሳው

ቄሮ በህብረት ካሰማው የአደባባይ መፈክር እኩል፤ ፋኖም ሆ ብሎ ወጥቷል። ኮንሶና ጋምቤላም የተቃውሞ ክንዶች ያለፍርሃት ተያይዘው አይተናል። ሁሉም ላይ ተተኩሷል። ሁሉም ላይ ካቴና ጠብቋል። የመቀሌ ወጣት ከነቀምቴው እኩል በህወሓት ላይ አንጀቱን ቆርጧል። ከዚህ ሁሉ የሚሰማ ድምጽ፤ የሚያንቀጠቅጥ ጩኸት ሌላ በየቤቱ የመሸገ የሚሊዮኖች ኩርፊያ ነበር። የሚሊየኖች ዝምታ በየጓዳው ነበር። ህወሓትን በኩርፊያ የገዘገዘ፤ ከራሱም ከሰፊው ህዝብም ሚሊዮን ጉልበት ነበር። ጃዋር ይሄንን አያደንቅም። ለዚህ እውቅና አይሰጥም። ብቻውን ስለሰራው ካልኩሌተር ቀን ከሌት ስቱዲዮ ሆኖ ያወራል።  ሲያወራ ለባህርዳር ሰው አይጨነቅም። የጎንደር እናት መጽናናት የምትሻ አይመስለውም። የልጁዋን ዝቅዝቅ ነጣላ የእኔ ነው እያለ ይነተርካታል። በለቅሶ ወቅት ብቻውን ሰርግ ደግሶ ያንባርቃል።  የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ነው ይሄንን የሚያወራው። ቢሰጡት እንዴት ሊመራው እንዳሰበ ሮያል ፋሚሊውም አያውቀው።

ከህወሓት ጉድጓድ ዐቢይን ለመቅበር?

ህወሓትን በጣልክበት መዝሙር ዐቢይን ለመጣል መሞከር ከተራ ግብታዊነት ወይም የሀገሪቱን ፖለቲካ በጥልቀት ካለመረዳት ጋር ይያያዛል። ህወሓት ዘመኑን ሙሉ ራሱን ገዝግዞ ለመጣል የታገለ የወንበዴ ስብስብ ነው። የብልጠትም፤ የሞራልም፤ የንግስናም፤ የጥበብም፤ የመሳሳትም እድሎች ተሰጥተውት  ያልተጠቀመ አሳዛኝ ቡድን ነበር።

ይሄኛው ንቁ ነው። እንደህወሓት አላረጀም፤ አልጃጀም፤ አልደነቆረም። ህወሓት 27 አመት ቆይቶ ካስተናገዳቸው ፈተናዎች ሁሉ፤ ይሄኛው የለውጥ ሀይል በሁለት ዐመታት ውስጥ የተጋፈጣቸው ይበልጣሉ። የተቀናጁ የኢኮኖሚ አሻጥሮችና ጥቃቶች ተፈጽመውበታል፤ ሰላምና መረጋጋቱ በተጠናና በአውዳሚ መንገድ እንዲታወክ ሆኗል፤ እንደ ህወሓት አይነት ሴረኛና አጥፊ ቡድንን ከስልጣን አስወግዶ መቀሌ ገብቶ እንዲቀመጥ መፍቀድን የሚያህል ከባድ ጣጣም የለም፤ ተራ የነጋዴ ስብስብ የፈጠረውን የጥቅም ሰንሰለት በጣጥሶ ለመደላደል የነበረው ፍዳም ቀላል የሚባል አልነበረም፤ ሆነ ተብሎ በችግሮች እንዲተበተብና ለግጭቶች ተመቻችቶ የተቀመጠው ሀገሀራዊ መዋቅርም ለጠላቶች መንቀሳቀሻ ምቹ ሆኖ አገልግሏል፤ የተለያየ ጽንፍ ያየዙ የፖለቲካ ሀይሎችን አፍንጫው ስር አስቀምጦም የተለያዩ ተግዳሮቶችን ሲያስተናግድ አስተውለናል፤  የኮሮና ጉዳይ፤ የግድቡ ጉዳይ፤እና ሌሎችም መሰል ፈተናዎች፤ ያለፈና በማለፍ ላይ ያለ መንግስት በመሆኑ እንደተለመደው በሰልፍና በሳቦታዥ ማስወገድ ቀላል አይሆንም። አለማቀፋዊ፤ አህጉራዊና ቀጣናዊ ቅቡልነት ለአንድ መንግስት ስለሚሰጠው ማስተማመኛ ለጃዋር ማስተማር እንደሱ ሰው መናቅ ስለሚሆንብን እንለፈው።

ይህችን ነጥብ ለመቋጨት ያህል፤ አዲሱን ዐቢይ አህመድ ባረጁ ስልቶች መታገል ብዙም አዋጭ አይደለም።

ዐቢይን ከማንም ጋር ቢሆን ማዋከብ

ጃዋር ብዙ ስህተቶች ሰርቷል። ተወዳዳሪ ከሌላቸው ስህተቶቹ መካከል ግን በጸረ ኦሮሞነት ዐቢይን የከሰሰበት ዋናው ነው። ይሄንን ፊደል ከቆጠረም ካልቆጠረም ፖለቲከኛ የማይጠበቅ ቆሻሻ ጥፋት በመፈጸሙ ብቻ ጃዋር ዊዝደም የለሽ ፖለቲከኛ መሆኑን አሳይቷል። ዐቢይን በዚህ አይነት የዘቀጠ ፎርሙላ ከኦሮሞ ጋር ሊያቃቅር በመሞከሩ ብዙዎች ይታዘቡታል። ስለኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት፤ አመለካከትና ወቅታዊ እንዲሁም ታሪካዊ ሆኔታዎች ያለውን ደካማ ግንዛቤም አሳይቷል። ‘ለኦሮሞ ያዳላል’ እያሉ ቁም ስቅሉን ከሚያሳዩት ጎን ቆሞ፤ ‘በኦሮሞ ጠላትነት’ ሊያዋክበው ሲሞክር ታዝበናል።

ዐቢይ የሀገር መሪ ነው። ራሱ ጃዋር “ጫፉን እንዳትነኩት’ በሚለው (ማንም የነካው የለም) ፌዴራላዊው ስርአት፤ የምትመራን ሀገር ነው ዐቢይ የሚያስተዳድረው። የበርካታ አካላትን ጥቅምና ፍላጎቶች አቻችሎ ነው መምራት ያለበት። የተለያዩ  ተቃራኒ ሀሳቦችን የሚያስተናግድ ልብ የሚያሰፈልገው ሰው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አማራንም ሆነ ኦሮሞን፤ እንዲሁም ሌሎቹን ዜጎቹን የሚጎዳ፤ አጥፊ የሚባል ፕሮጀክት ያለው ሰው አይደለም። ዐቢይ ጊዜ ሰጥተው የሚመዝኑት አይነት ሰው ነው። ግራ በሚያጋቡና፤ አማራውም በዘረኝነት፤ ኦሮሞውም በዘረኝነት እኩል የሚከስሱት አይነት ሰው አይደለም። ይሄንን መረዳት ለጃዋር ከባድ አልነበረም። ራሱ ከአመታት በፊት በጨቅላ የፖለቲካ ዘመኑ የተቸውን አካሄድ ዛሬ ለስልጣን ግቡ ሲል ሲጠቀመው አይተናል። ‘ሳይኖር የሞተ’ የምንለው ለዚህ ነው።